ባሕር ዳር: ነሐሴ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሻደይ ባሕላዊ ጨዋታ ከነሐሴ 16/2016 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም ድረስ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በድምቀት የሚከበር በተለይም የልጃገረዶች የድምቀት በዓል ነው። ሻደይ መሠረቱ ከክርስትና ሃይማኖት ጋር የተያያዘ ሲኾን ባሕላዊ ይዘቱን ሳይቀይር ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ በትውልድ ቅብብሎሽ የመጣ በዓል ነው።
በበዓሉ ወቅት:-
አሽከር ይሙት ይሙት ይላሉ የኔታ፣
አሽከር አይደለም ወይ የሚኾነው ጌታ።
ሻደይ ሻደይ ወይ….. እያሉ ልጃገረዶቹ በዓሉን በዜማ ያደምቁታል።
ልጃገረዶች የነጻነት በዓላቸው ነውና ሻደይን ዓመቱን ሙሉ በጉጉት የሚጠብቁት ባሕላዊ ጨዋታ ነው። ቤተልሄም ወርቁ የጻግቭጂ ወረዳ ነዋሪ ስትኾን ሻደይን ከልጅነቷ ጀምሮ እየተጫወተች እንዳደገች ትናገራለች።
ሻደይን ለማክበርም “ጥብቆ” የተባለውን ባሕላዊ ልብሷን በማጥቆር እና በመጥለፍ፣ ድኮት እና ሽኳሯን በመወልወል እንዲሁም ጉትቻዋን በማዘጋጀት፣ ድሪ እና ማርዳዋን በመጎንጎን ዓመቱን ሙሉ ለሻደይ በቂ ዝግጅት እንደምታደርግ ገልጻለች።
“ሻደይ ለዋግ ቆነጃጅቶች እና ልጃገረዶች የነጻነታችን ቀን ነው” ያለችው ቤተልሄም የዘንድሮውን የሻደይ በዓል በደማቅ ኹኔታ ለማክበር መዘጋጀቷንም ነው ያስረዳችው።
ሻደይ የሴቶች በዓል ቢኾንም ወንዶችም ልጃገረዶቹን ከክረምት ጎርፍ በመጠበቅ እና የወደፊት የትዳር አጋራቸውን ለመምረጥ አምረው እና ተውበው እንደሚያከብሩት ወጣት አፈወርቅ በላይ ተናግሯል።
የጻግብጂ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዋኘው ደባሽ በወረዳው ኹሉም አካባቢዎች በዓሉ እንደሚከበር ገልጸዋል። ለዚህም በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው ለአሚኮ ያስረዱት።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች አለመከበሩን የገለጹት ኀላፊው የዘንድሮውን በዓል በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን አስገንዝበዋል፡፡
“ሻደይ ለዘላቂ ሰላማችን እና ለአንድነታች” በሚል መሪ መልዕክት በብሔረሰብ አሥተዳደር ደረጃ በሰቆጣ ከተማ እንደሚከበር የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ጣምተው ገላስ ገልጸዋል። የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!