ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መገኛው በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ነው። ጮቄን ተንተርሶ የተመሰረተው ሙሉ ኢኮሎጂ ሁሌም አረንጓዴ ምድር ነው። መገኛ ቦታው በጣም ቀዝቃዛና ረግረጋማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጮቄ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ በአማካኝ 4100 ሜትር ከፍታ ያለው ጮቄ በተለምዶ የጎጃም ጣራ በመባል ይጠራል፡፡
የጮቄ ተራራ ሰፊ ተፋሰስ የሚሸፍን ሲሆን ሰባት የሚሆኑ የምሥራቅ ጎጃምና ምዕራብ ጎጃም ወረዳዎችን ያዋስናል። ከነዚህ ወረዳዎች መካከል በምዕራብ ጎጃም የሚገኘው የደጋ ዳሞት ወረዳ አንዱ ነው።
ደጋ ዳሞት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር አሸናፊ የሆነ የሙሉ ኢኮ ሎጅ መገኛ ነው። የቪዚት አማራ መረጃ እንደሚያመላክተው በገነት የተፈጥሮ ሀብት ቱሪዝም ኅብረት ሥራ ማኅበር የሚተዳደረው ሙሉ ኢኮ ሎጅ ማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝምን በማስፋፋት እና አካባቢን በመጠበቅ በመጀመሪያው የድንቅ ምድር የእውቅና እና ሽልማት መረሃ-ግብርም አሸናፊ ነው። አካባቢው እውነትም በድንቅ ምድር ላይ ያረፈ ድንቅ ሎጅ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!