ባሕር ዳር: ነሐሴ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ውበት እንደ አፍላጉ እንደ ግዮን ይፈስስበታል፤ ታሪክ እንደ ተራራው እንደ ራስ ደጀን ከፍ ብሎ ይኖርበታል፤ ባሕል እንደ ጀምበር ያበራበታል፤ ሃይማኖት እንደ ዓለት ይጠነክርበታል፤ ያለመናወጽ ይጸናበታል፤ እሴት እንደ አደይ አበባ ያብብበታል፡፡
በውበቱ ምድር፣ በታሪኩ አድባር ጠቢባን አበው በሐይቅ ላይ ደብር ደብረዋል፣ ገዳም ገድመዋል፣ ዓለም የማይደርስባቸው፣ ሳይንስ የማይፈታቸው ጥበባትን አስቀምጠዋል፤ በዋሻ ውስጥ የረቀቀ ምስጢር አኑረዋል፤ አለትን እንደ አሽከር አዝዘዋል፤ ጣሪያ ሠርተው መሠረት አውጥተዋል፣ የዓለሙን ጥበብ ሁሉ ንቀው አዲስ ጥበብ ለዓለም አሳይተዋል፤ በአንድ ቋጥኝ የረቀቁ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል፣ ጡብ ደርድረው የተዋቡ አብያተ መንግሥታትን ሠርተዋል፣ በመጻሕፍት የተጻፉትን በኪነ ሕንጻ ገልጠዋል፡፡ በምድሪቷ ከውበት ላይ ውበት ደራርበዋል፤ እጹብ ድንቅ የተባሉ መስጅዶችን አሳምረው ገንብተዋል፡፡
በአብያተ መንግሥታቱ መንግሥታዊ ሥርዓትን አጽንተዋል፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገዋል፤ ታላቅ ሀገርን ለትውልድ አስረክበዋል፤ በየገዳማቱ፣ በየአድባራቱ እና በየመስጊዶቹ ለትውልድ ምግባርን፣ ፍቅርን፣ እንድነትን፣ ደግነትን፣ ለሰው ሲሉ ራስን አሳልፎ መስጠትን አስተምረዋል፡፡
ፊደል ቀርጸዋል፤ ብራና ፍቀው፣ ብዕር አሹለው፣ ላባ አዘጋጅተው፣ ቀለም በጥብጠው፣ ታሪክ ጽፈዋል፣ ተፈጥሮ ላስጌጠችው ምድር ሌላ ጌጥ ፈጥረዋል፡፡ ዐይኖች ሁሉ ለማየት የሚጓጉለት፣ ጀሮዎች ሁሉ ለመስማት የሚያዘነብሉለት፣ እጆች ሁሉ ለመዳሰስ የሚዘረጉለት፣ እግሮች ሁሉ ለመርገጥ የሚራመዱበት ደግነት፣ ሰው አክባሪነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ጀግንነት የበዛበት ድንቅ ምድር፡፡
ውኃ በውኃ ላይ የሚያልፍበት፣ ድንቅ የተፈጠሮ ኅብር የበዛት፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች የበረከቱበት፣ ታላላቅ ታሪካዊ ሥፍራዎች ያሉበት ምድር ነው የአማራ ክልል፡፡ በዓለማዊ እይታ እና ጥናት የዓለም ረጅሙ፣ በመንፈሳዊ ዕይታ ከተቀደሱ እና ከተመረጡ አፍላጋት መካከል አንደኛው ግዮን ( ዓባይ) የሚፈልቅበት፣ ተመርምሮ የማይዘልቅ ዕውቀትን፣ ጥበብን፣ ፍልስፍናን፣ ሃይማኖትን፣ ታሪክን እና እሴትን የያዘው ጣና ያረፈበት፣ የበረሃው ዘብ አልጣሽን ጨምሮ ብዛት ያላቸው ፓርኮች፣ ጥብቅ ደኖች የሚገኙበት፣ በየተራራው እና በየጋራው፣ በየሜዳው እና በየሸለቆው ተነግሮ የማያልቅ ታሪክ የሚገኝበት ምድር ነው፡፡ ይህ ምድር ጎብኝዎች ይጎበኙት ዘንድ የሚመኙት፣ የታሪክ አጥኝዎች፣ የባሕል ተመራማሪዎች፣ የአንትሮፖሎጂ አሳሾች፣ የአርኪዎሎጂ ቆፋሪዎች፣ የሥነ ጽሑፍ ጠበብቶች ለምርምር የሚፈልጉት፣ የሚመኙት፣ የሚመርጡት ነው፡፡
ታዲያ በዚህ ድንቅ ምድር ያለውን ሃብት ለማሳየት ሰላም ይፈትነዋል፡፡ ጎብኝዎች እንደ ፍላጎታቸው እና እንደ ምኞታቸው እንዳያዩ ያደርጋቸዋል፡፡ የተረጋጋ ሰላም ባገኘ ጊዜ ደግሞ ጎብኝዎች ይጎርፉበታል፡፡ የእስካዛሬዎቹ የሰላም እጦቶች ተስተካክለው ጎብኝዎች በሰላም ወደ አማራ ክልል እንደሚመጡም ተስፋ ተጥሏል፡፡
የቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢው ቱሪስት አስጎብኝ ማኅበር ሊቀ መንበር እስታሉ ቀለሙ ሰላም መጥቶ ድንቅ የኾኑ አካባቢዎች ለዓለም እያሳዩ በቱሪዝም ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ያላቸውን ተስፋ ይገልጻሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው ድንቅ ቅርስ ባለቤቶች በመኾናችን የቱሪዝም ተጠቃሚዎች ነበርን፤ ነገር ግን ከኮሮና ቫይረስ ጀምሮ ያለው ችግር ከቱሪዝም ይገኝ የነበረውን ገቢ ቀንሶታል፤ የላሊበላ ነዋሪዎች በእጅጉ ተፈትነዋል፤ በተለይ ደግሞ አስጎብኝዎች በከፋ ችግር እያለፉ ነው ይላሉ፡፡
ውብ ምድር አለ፣ ድንቅ ቅርስ ይዞ መቸገር የተገባ አይደለም፣ ችግሮች ተቀርፈው ወደ ቱሪዝም እንቅስቃሴ መሄድ አለብን ነው የሚሉት፡፡ በወርሐ ነሐሴ የሚከበሩ በዓላትን ጨምሮ በተከታታይ የሚከበሩ በዓላት የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ያነቃቃሉ የሚል ተስፋም አላቸው፡፡ ተስፋችን እንዲለመልም፣ ድንቁን ሃብታችን ለዓለም እያሳየን፣ ታሪካችን ለዓለም እንድንነግር፣ ሃብትም እንድናገኝ ለሰላም መሥራት ይጠበቃልም ይላሉ፡፡ ሁሉም ስለ ሰላም እንዲዘምርም ጠይቀዋል፤ ይህ ከኾነ በ2017 እንግዶች ይመጣሉ፣ እኛም እንጠቀማለን ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ ክልሉ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች በስፋት ያሉበት፣ በተፈጥሮ የታደለ ነው ይላሉ፡፡ ከዳር እስከ ዳር ተነግሮ እና ተቆጥሮ የማያልቅ ሃብት ያለው፣ ተከታታይ የኾኑ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት የሚከበሩበት ነው ይሉታል፡፡ የክልሉን ሃብት ለማስተዋወቅ፣ ጎብኝዎችን ለመሳብ፣ የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት በዕቅድ የሚመራ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የክልሉን የቱሪዝም ሃብት የሚያስተዋውቅ መጽሐፍ ተጽፏል፣ ከዚያም ባለፈ በሚዲያ የማስተዋወቅ ሥራው ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
በዓላት የማኅበረሰብ የታሪክ እና የማንነት መገለጫ ኾነው እንዲቀጥሉ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል፡፡ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶችን የመለየት፣ የመመዝገብ እና የመጠበቅ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት፡፡ የቱሪዝም ሃብቶችንም እናለማለን ብለዋል፤ በሙዚዬም መቀመጥ የሚገባቸው ቅርሶችን በሙዚዬም የማስቀመጥ ሥራም እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡ የቱሪዝም ምጣኔ ሃብት ለሀገር ዕድገት አስፈላጊ ነው፣ ይሄ ደግሞ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፤ በአማራ ክልል ሰፊ ሃብት አለን፣ ሃብቱን ለመጠቀም ደግሞ ለጎብኝዎች ምቹ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት ከተቻለ ተዝቆ የማያልቅ ሃብት ይገኝበታል ይላሉ፡፡ በወርሐ ነሐሴ ጀምሮ የሚከበሩ በዓላት ላይ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው የእንግዳ አቀባበል መቀበል እና ቆይታቸውን ያማረ ማድረግ ይጠበቃል፤ ለሁሉም ደግሞ ሰላም ያስፈልጋል፣ ሰላም የሁሉም ነው፣ በዓላቱን በሰላም ለማክበር፣ ሃብትን ማስተዋወቅ እና ስለ ሰላም መሥራት ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ ስለ ምን ቢባል ታላቅ ሃብት ያለውን ክልል የሰላም እጦት የሚገባውን እንዳያገኝ አድርጎታልና፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኝዎች የሚጎርፉበት፣ ሃብት የሚፈስስበት፣ ምጣኔ ሃብት የሚያድግበት እንዲኾን ሰላም ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ሰላም ከሌለ መልካሙን ምድር፣ ድንቁን አድባር ክፉ ነገር ያጠላበታልና፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!