ደብረ ማርቆስ: መሥከረም 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በቱሪዝም ዘርፍ የኅብረተሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሃይማኖታዊ ቦታዎችን የማስተዋወቅ፣ ቅርሶችን የመጠበቅ እና የማልማት ሥራዎችን ሢሠራ ቆይቷል። የፀጥታ ችግሩ በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ሲሆን ይህም ከዘርፉ ሊገኝ የሚችል ጥቅም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የከተማ አሥተዳደሩ ባሕልና ቱሪዝም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ የውልሰው ወርቅነህ ተናግረዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ያሉት ሲሆን ገዳማት፣ ቀደምት የቤተ መንግሥት ሕንጻዎች እና ቅርሶች ተጠቃሾች ናቸው። ኅብረተሰቡ ባሕሉን እና እሴቱን የሚገልጽባቸውን እነዚህን ሃብቶች መጠበቅ እና መንከባከብ እንዳለበትም ኃላፊዋ አሳስበዋል።
ሰላም ለቱሪዝም ዘርፍ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ በመኾኑ ኅብረተሰቡ ለሰላም እና ለአብሮነት ድርሻውን ማበርከት እንዳለበት ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።
በየዓመቱ መስከረም 16 እና 17 የሚከበረውን የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ እና አብሮነትን በጠበቀ እሴት ለማክበር ዝግጅት መደረጉንም ነው ኃላፊዋ የገለጹት።
የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መንገድ በሰላም እንዲከበር ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም የከተማው ነዋሪ ትብብር እንዲያደርጉም ኃላፊዋ ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!