የማንነታችን ማሳያ የኾነው ቅርስ ትኩረት ይሻል!

0
228

ባሕር ዳር: መሥከረም 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅርስ መዝገብ ላይ በዓለማችን ሊጎበኙ ከሚገባቸው ቅርሶች ውስጥ በቀዳሚነት ሰፍሯል – የጎንደሩ ደብረብርሃን ሥላሴ፡፡ የጎንደሩ ደብረብርሃን ሥላሴ በያዛቸው ቅርሶች ምክንያት ዓለም አቀፉ ተቋም አምኖበት በመዝገቡ አስፍሮ ዓለም ላይ ያሉ ቱሪስቶች እንዲጎበኙት ከሚመክራቸው አካባቢዎች ተጠቃሹ ነው።

ቅርሱን ለመጎብኘትም በርካታ ቱሪስቶች ከዓለም የተለያዩ አቅጣጫዎች እየመጡም የሚጎበኙት ቅርስ ኾኖ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ ይህ ለሀገርም ለዓለም ሕዝብም ሃብት እና ኩራት የኾነው ቅርስ ጉዳት ላይ እንዳለ እና በየጊዜው ቅርሱ እየተጎዳ ስለመሄዱ የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ፡፡

የጎንደር ደብረብርሃን ሥላሴ የገዳሙ አባቶች የቅርሱ ጉዳት ተባብሶ የህልውና አደጋ ውስጥ ከመግባቱ በፊትም ሀገሪቱም ኾነ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ቅርሱ ያለበትን ኹኔታ ተመልክተው አስፈላጊውን ጥገና እንዲያደርጉለት ጠይቀዋል፡፡ በአማራ ክልል የባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጋሻየ መለሰ እንዳሉት ጎንደር ደብረብርሃን ሥላሴ በጎንደር በዩኔስኮ ከተመዘገቡት ዘጠኝ ቅርሶች መካከል አንዱ ሲሆን አሁን ላይ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ጉዳት እንደደረሰበት ነው የተናገሩት፡፡

ቅርሱ በእርጅና፣ በፍሳሽ እና በአያያዝ ጉድለት ጉዳት እንደደረሰበት የተናገሩት ዳይሬክተሩ ቢሮው ቦታው ድረስ ተገኝቶ የጉዳቱን መጠን ስለመመልከቱም ነው የጠቆሙት፡፡ ቢሮው ከፌዴራል ቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመኾን ቅርሱ ያለበትን ኹኔታ እና መጠገን እንዳለበት ለዩኔስኮ ማሳወቅ እንደሚገባ ገልጸው ይህ ሥራም እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ቅርሱ የሕልውና አደጋ ውስጥ ያን ያክል ገብቷል ባይባልም ግን ያለበት ኹኔታ ችግር ውስጥ በመኾኑ በተሠራበት አግባብ መጠገን እንደሚገባውም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ቅርሱን ለመጠገን በቢሮም ደረጃ መጠገን የሚችሉ ስድስት ባለሙያዎች እንዳሉ ገልጸው ጥገናውን ለማድረግ ግን ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያውቀው ማድረግ እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡

ዩኔስኮ ቅርሱ እንዲጠገን ባይከለክልም፣ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ግን ማወቅ እንደሚፈልግ ነው ያብራሩት፡፡ የቅርሱ ኹኔታ አሁን ላይ የጉዳቱ መጠን እየተጠና እንደኾነ እና ቅርሱን ለመጠገን ከሀገሪቱ አቅም በላይ የሚኾን ከኾነ እገዛ ከዩኔስኮ እንደሚጠየቅም አስገንዝበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here