የልደት በዓልን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ እንደኾነ የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዋና አሥተዳዳሪ ገለጹ፡፡

0
236

በላሊበላ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደኾነ የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዋና አሥተዳዳሪ አባ ሕርያቆስ ጸጋየ ገልጸዋል። ዋና አሥተዳዳሪው ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ክብረ በዓሉ ምዕመናን በረከት አግኝተው የሚሄዱበት በዓል እንዲኾን አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

”በቦታው ተገኝቶ በመሳለም ከሚገኝ መንፈሳዊ ፍሬ ባሻገር ሁሉም ሰው በዓመት አንድ ጊዜ ስፍራውን መጎብኘት ባሕል ኾኗል” ያሉት የገዳሙ አሥተዳዳሪ ጎብኚዎች በበዓሉ ሰሞን ከየማዕዘናቱ መጥተው በበዓሉ እንደሚካፈሉም አስረድተዋል።

በዓሉ ለእምነቱ ተከታዮች መንፈሳዊ እርካታ መኾኑን እና ከእምነቱ ዉጭ ለኾኑትም ጥበብን የሚያደንቁበት እንደኾነ አባ ሕርያቆስ አመላክተዋል። እናም ኹሉም ሰው ስፍራውን እንዲጎበኘው ጋብዘዋል።

”የኮቪድ ወረርሽኝ እና የሰሜኑ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት የነበረው የጎብኚዎች ፍስሰት አሁን ላይ እንደማይታይም አስረድተዋል፡፡ አሁንም በአካባቢው አልፎ አልፎ በሚከሰተው ግጭት ምክንያት አካባቢው ጥሩ ያልኾነ ገጽታ እየተሰጠው ቱሪስቶችም እንዳይመጡ ሰበብ እየኾነ ነው ብለዋል። የጎብኚዎች ፍስሰት በመቀነሱም ከ600 በላይ የደብሩ አገልጋይ ሊቃውንት፣ ካህናት እና ዲያቆናት እየተቸገሩ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ሌላው ማኅበረሰብም እንደተቸገረ ነው የገለጹት።

የአካባቢው ነዋሪዎች የኑሮ መሰረት በቱሪስት ፍስሰቱ ላይ የተመሰረተ እና በአንድም በሌላም ሁኔታ ከቦታው ተጠቃሚ እንደኾኑ ነው የገዳሙ አሥተዳዳሪ ያስረዱት።

አሁን ላይ በላሊበላ ሰላም መስፈኑን ገልጸው በመጪው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የጎብኚዎች ፍስሰት እንዲጨምር ሁሉም የበኩሉን እንዲያበረክት ጠይቀዋል።

በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ እና የተቀዛቀዘው የአካባቢው የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲመለስ ሁሉም ወደ ግጭት የገቡ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ አባ ሕርያቆስ ጠይቀዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here