ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሌሎች ያልያዟቸውን ይዟል፣ የሚናፍቋቸውን ብርቅዬዎች ታቅፏል፣ ለብርቆቹ ቤታቸው፣ ዓለማቸው ነው፡፡ ዓይኖች ሊያዩት የሚወዱት፣ ብዙዎች የሚደነቁበት፣ አብዝተውም የሚገረሙበት፣ በውበቱ ሊዋቡበት፣ በግርማው ሊደነቁበት፣ ከሰገነቱ ላይ ቆመው ተፈጥሮን ሊያደንቁበት የሚፈልጉት ታላቅ ሥፍራ፡፡
ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ ታላቅነቷን የምትገልጥበት፣ ከፍታዋን የምታሳይበት፣ በሌሎች ዓለማት የማይገኙ ብርቅየዎችን ጠብቃ ያኖረችበት፣ ከዓለም የተለየች እና የረቀቀች መኾኗን የምታስመሰክርበት፣ ተፈጥሮን ከእነ ወዙ የምትገልጥበት፣ ውበትን ከእነ ክብሩ የምታሳይበት፣ የዓለምን ቀልብ የምትስብበት ድንቅ ነው፡፡
ይህ ሥፍራ ኢትዮጵያ ብርቆችን የምትጠብቅበት፣ ለትውልድም የምታሸጋግርበት አስገራሚ ነው፡፡ እርሱን የሚመስል ውበት የተቸራቸው፣ እርሱ የያዛቸውን ሃብቶች የተሰጣቸው ሌሎች ሥፍራዎች ከየትም አይገኙም፡፡ አምሳያ የሌለው ውብ ነውና፡፡
ሰማይን ተደግፈው የቆሙ የሚመስሉት ተራራዎች፣ በተራራዎች አናት ላይ እየተነሱ ወደ ታች የሚምዘገዘጉ ምንጮች፣ በገደሉ ላይ ያሉ የማይደረስባቸው ለምለም ሳሮች፣ የማይነኩ ዛፎች ቀልብን ይስባሉ፣ ከፍታን ይነግራሉ፣ በተራራዎች አናት፣ በሸለቆዎች ስርጥ ለሰርጥ፣ በሚያስፈራው ገደላማ ሥፍራ የሚመላለሱት ብርቅዬ እንስሳት ደስታን ይሰጣሉ፤ ዐይንን ያሳሳሉ፤ በተራራዎች አናት ላይ ባዘቶ እየመሰለ የሚጎተተው ደመና እጹብ ያሰኛል የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፡፡
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ኢትዮጵያን ድንቅ ከሚያሰኟት፣ የዓለም ጎብኝዎች ከሚሳቡበት፣ ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ ዘንድ ከሚጓጉለት የፈጥሮ ሃብቶች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡
በውስጡ የያዛቸው የቀይ ቀበሮ እና የዋልያ እንስሳት ደግሞ ሌላኛው ውበቶቹ፣ ሌላኛው መለያው ናቸው፡፡ ይህ ታላቅ ሥፍራ የምድር ሰገነት፣ የማያረጅ ውበት ነው፡፡ ለዘመናት ምድርን እንደሰገነት ኾኖ እያሳያት፣ ውበቱ ሳያረጅ እና ሳይጠወልግ እንዳስዋባት ኖሯልና፡፡
ሀገር ሰላም ስትኾን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጎብኝዎች ወደ ስሜን ተራራዎች ያቀናሉ፡፡ በደረሱም ጊዜ በዚያ ለሰማይ የቀረበ በሚመስለው፣ ቅዝቃዜ በማይለየው ሥፍራ ብርቅዬ እንስሳትን እየተከታተሉ ይሰነብታሉ፡፡ ሀገር ሰላም ባልኾነች ጊዜ ግን ጎብኝዎች እየናፈቁት፣ እንግዳ ተቀባዮቹ የስሜን ሰዎችም እንግዶችን እየናፈቁ ተለያይተው ይኖራሉ፡፡
ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው የአማራ ክልል ግጭት የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ጎድቶታል፡፡ በቱሪዝም ቀጥተኛ ተጠቃሚ የነበሩ ወገኖች ተጎድተዋል፡፡
ለወትሮው በጎብኝዎች ይጨናነቁ የነበሩ አካባቢዎች ጎብኝዎችን ናፍቀዋል፡፡ ጎብኝዎችን ከናፈቁ አካባቢዎች መካከል ደግሞ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አንደኛው ነው፡፡
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የተፈጥሮ ሃብት፣ የቱሪዝም ልማት እና ግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበር ሥራ አሥኪያጅ ቄስ ሞገስ አየነው ብዙ ጎብኝዎች ይመጡበት የነበረው ሥፍራ አሁን ላይ እንግዶች አይመጡበትም፣ አሳዛኝ ነው፣ ከ2012ዓ.ም ጀምሮ የጎብኝዎች እንቅስቃሴ ተጎድቷል ነው ያሉት፡፡ በክልሉ ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ደግሞ በጣም የከፋ ነው ይላሉ፡፡
በማኅበራቸው አማካኝነት ለጎብኝዎች በቅሎ ያከራዩ እንደነበር ያስታወሱት ቄስ ሞገስ ጎብኝዎች በስፋት ይመጡ በነበረበት ጊዜ በሚከራዬው በቅሎ እንጠቀም ነበር፤ አሁን ግን ይሄ ሁሉ የለም ነው ያሉት፡፡
ሰላሙ በጣም ጎድቶናል፣ ከሁሉ አስቀድሞ ትልቁ ሃብት ሰላም ነው፣ ለቱሪዝም ወሳኙ እና አስፈላጊው ሰላም ነው፣ ሰላም ባለመኖሩ ስናገኘው የነበረውን ገቢ አጥተናል ነው ያሉት፡፡ ማኅበሩ 8 ሺህ 100 አባላት አሉት፡፡ በዚህ ማኅበር ይጠቀሙ የነበሩ ሁሉ አሁን ችግር ላይ ናቸው ነው የሚሉት፡፡
በቅሎ የሚያከራይ፣ አጃቢ፣ ድንኳን ጣይ፣ አስጎብኝ ሁሉም ተጎድቷል፤ የተለመደውና መተዳደሪያ የኾነው ሁሉ ሲቀር ብዙዎች እቃ እየሸጡ የቀን ሥራ ለመሥራት ተገድደዋል ይላሉ፡፡
ሰላም በነበረበት ጊዜ እና ጎብኝዎች በሚመጡበት ወቅት ተጠቃሚዎች ነበርን፣ ቤተሰብ እናስተዳድርበት፣ ዘመድ እናግዝበት ነበር አሁን ግን ሁሉም የለም ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ነገር መልካም እንዲኾን ሁሉም ለሰላም አንድ መኾን አለበት፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲጠናከር የጋራ አቋም ሊያዝበት ይገባል ይላሉ፡፡
የቱሪዝም እንቅስቃሴው ሲዳከም ለብርቅዬ እንስሳት የሚደረገው ጥበቃም እንደሚቀንስ ነው የተናገሩት፤ እኛ ከአባቶቻችን እንደተረከብነው ሁሉ፣ እኛም ለልጆቻችን ማስረከብ ስላለብን ፓርኩ መጠበቅ አለበት ነው የሚሉት፡፡
ፓርኩ የሚጠበቅ ሰው ከፓርኩ ሲጠቀም ነው፣ ከፓርኩ ጥቅም ሲያጣ ግን ጥበቃውን ችላ ይለዋል፣ እኛ ግን ይህ ጊዜ ያልፋል፣ መልካም ጊዜም ይመጣና እንደ ወትሮው እንጠቀማለን፣ ስለዚህ ፓርኩ በችግር ጊዜ ተጠብቆ መቆዬት አለበት፣ በችግር ጊዜ ካልጠበቅነው በሰላም ጊዜ የሚሰጠንን ጥቅም አናገኝም እያልን እያስተማርን ነው ብለውናል፡፡
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ዋልያ አስጎብኝ ማኅበር ሊቀመንበር ካሳ ብርሃኔ የሰላም እጦቱ በቱሪዝሙ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ለመግለጽ የሚከብድ ነው ይላሉ፡፡ ተጽዕኖው ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቡናዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ነው፤ መጀመሪያ በኮሮና ቫይረስ፣ ከዚያም በስሜኑ ጦርነት፣ አሁን ደግሞ በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ቱሪዝም ስለቀዘቀዘ ገቢያችን ቆሟል ነው ያሉት፡፡
ለከፋ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ተዳርገናል ነው የሚሉት፡፡ አብዛኞቻችን ከፓርኩ ውስጥ የወጣን ስለኾነ ቤተሰቦቻችንም ለችግር ተጋልጠዋል ነው ያሉት፡፡
ገቢ በነበረን ጊዜ ለመንግሥት ግብር የምንከፍል፣ ቤተሰቦቻችን የምንረዳ፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎች የምንሳተፍ ነበርን አሁን ግን ችግር ላይ ነን ብለዋል፡፡
ከዛሬ ነገ ይሻላል እያልን ተስፋ ሰንቀን፣ በደህናው ጊዜ ያስቀመጥናትን ገንዘብ እያወጣን እዚህ ደርሰናል፣ ለአንድ ዓመት የሚኾን ደግሞ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ረድተውናል፤ ሌላውን ግን በራሳችን ጥረት ነው ያለነው ይላሉ፡፡
በሰላም እጦት ምክንያት እንደ ሀገር ሰበዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አለ፤ ከቱሪዝም ጋር በቀጥታ የምንገናኝ ሰዎች ደግሞ በእጅጉ ተጎድተናል፤ ሰላም ምን ያክል እንደሚያስፈልገን ስለምናውቅ እንደ ማኅበር ለሰላም ተግተን ነው የምንሠራው ብለዋል፡፡
ሰላም የሚመጣው ሰላምን ስለፈለግን እና ስለ ሰላም ስላወራን አይደለም፣ ሰላም የሚመጣው ሁሉም በቁርጠኝነት ሢሠራ፣ በመወያየት፣ በሰላም እጦቱ ምን ያክል ሕዝብ እየተሰቃየ እንደኾነ በማወቅ እና በመረዳት ነው ይላሉ፡፡
ሰላም ባለመኖሩ ስቃዩ እየተራዘመ ያለው ሕዝብ ነው፣ ሁሉም ለሰላም እጁን መዘርጋት አለበት፣ ሰጥቶ በመቀበል መወያየት እና መደራደር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ለሕዝብ እቆማለሁ የሚል ሁሉ ለሕዝብ ማሳብ እና ሰላምን ማስቀደም አለበት ይላሉ፡፡ የሰላም እጦቱ ለሰዎች ብቻ አይደለም፣ በፓርኩ ላሉ ብርቅየ እንስሳትም አደጋ ኾኗል ነው ያሉት፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጥቂት የሰላም ተስፋ ስለታየ እንግዶች መምጣት ጀምረዋል ብለዋል፡፡ ቱሪስቶች መምጣት በመጀመራቸው ደግሞ አስጎብኝዎች ብቻ ሳይኾን ከተማዋም ደስተኛ ናት፤ እንኳን ደስ አላችሁ እየተባባልን ነው ይላሉ፡፡
ሰላም እንዲረጋገጥ መምጣት የጀመሩ ጎብኝዎች በስፋት እንዲመጡ ለማድረግ ሁሉም ለሰላም መሥራት አለበት፣ ሰላም ተረጋግጦ ሠርተን የምንበላበት በሰላም ወጥተን የምንገባበት ጊዜ እንዲመጣ እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡ ከያዘው ልቀቀው ወጥቶ ለሰላም መዘመር ይገባል ብለዋል፡፡
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማሩ ቢያድግልኝ የቱሪዝም ፍሰቱ ከኮሮና ወረርሽኝ ጀምሮ እንደቀነሰ ነው የተናገሩት፡፡ ከከኮሮና ወረርሽኝ ሳያገግም የተከሰተው ጦርነት ወደ ሌላ ችግር እዳስገባውም አስታውሰዋል፡፡
ከሰሜኑ ጦርነት ማግሥት ጥቂት መነቃቃት ሲፈጠር ደግሞ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሙሉ ለሙሉ ወደ ማስቆም ደረጃ አድርሶት መቆየቱን ነው የገለጹት፡፡
በቅርቡ በተፈጠረው የሰላም ተስፋ ከመስቀል በዓል ወዲህ ደግሞ ጎብኝዎች መምጣት መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡ ለመምጣት ፕሮግራም እያስያዙ ያሉ መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡
የሰላም ተስፋው እየሰፋ ከሄደ የጎብኝዎች እንቅስቃሴም እንደሚቀጥል ነው ያመላከቱት፡፡ ሰላሙን ማስፋት እና ተጎድተው የኖሩ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ያለው ተስፋ ወደኋላ እንዳይመለስ በጥንቃቄ መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡ ፓርኩን ልዩ ጥበቃ በማዘጋጀት እየጠበቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ፓርኩን መጠበቅ ዋናው ጉዳይ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
ቱሪዝም ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው ያሉት ኀላፊው ሁሉም ለሰላም መሥራት አለበት ብለዋል፡፡ በአንድ ወቀት ለማስተናገድ እስከሚያስቸግር ድረስ ጎብኝዎች ይመጡ እንደነበርም አስታውሰዋል፤ ወደዚያ ወቅት ለመመለስ ለሰላም መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ለብሔራዊ ፓርኩ ሁሉም ትኩረት ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል፡፡ ስሜን ተራራዎች የብዙ ሃብት ባለቤት በመኾኑ ጥበቃ እና ክብካቤ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!