ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቡልጋ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች አንዷ ናት። መልካ ምድራዊ ገጽታዋ ወይና ደጋ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ ዋና ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ቦታዎች መካከል አንዷ ተደርጋ ትወሰዳለች።
አብዛኛውን ጊዜ የመካከለኛው ዘመን ነገሥታት መናገሻ ተደርጎ ይወሰድ ከነበረው ተጉለት ጋር የተሳሰረ በመኾኑ “ተጉለት እና ቡልጋ” በሚል በጋራ ሲዜምላቸው ይደመጣል።
በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት አብዛኛው ሠራዊት ከተጉለት እና ቡልጋ የተሰባሰበ እንደ ነበር አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊያን ጽፈዋል። የምኒልክ ምሽግ እና የጦር ግምጃ ቤት መገኛም እዚሁ ቡልጋ ነው።
ቡልጋ በኢትዮጵያ እንደ ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሐብተወልድ፣ ጸሐፊ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮኃንስ፣ ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድሕን፣ ብላቴን ጌታ ማሕተመ ሥላሴ ወልደመስቀል፣ ተስፋ ገብረሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ፣ ተክለጻዲቅ መኩሪያ፣ ደጃዝማች ሐብተ ሥላሴ በላይነህ፣ ሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ እና የመሳሰሉ ታላላቅ ሊቃውንትን ያፈለቀች ቦታ ናት። ቡልጋን መጎብኘት የታላላቅ እሳቤ ሰዎችን መገኛ ለማየት እና በውብ መልክዓ ምድር ላይ ተገኝቶ ተፈጥሮን ለማድነቅም እድል ይሰጣል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!