ባሕር ዳር: ኅዳር 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የጥንት ሥልጣኔ እና የዕምነት ሀገር ለመኾኗ ምስክር የሚኾኑ ዘመናትን ያፈራረቁ እና የዘለቁ ምልክቶች አሏት። የጎንደር አብያተ መንግሥታት ፣ የጣና ገዳማት፣ የአክሱም ሐውልት እና የቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ጎላ ብለው የምንሰማቸው፣ ያየናቸው፣ የዳሰስናቸው እና የተደመምንባቸው ናቸው ።
ሌሎች በስፋት ያልተወራላቸው የትላንት ማንነታችን መነጽር የኾኑ የዘመን ዥረት ያላደበዘዘባቸው ሃብቶች አሉን። በዚህ ጽሑፍ ልናነሳ የወደድነው ከላሊበላ ከተማ በሰሜን አቅጣጫ 42 ኪሎ ሜትር ተጉዘን ስለምናገኘው ድንቅ መንፈሳዊ ስፍራ ነው። የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ለማየት የመጣ ጎብኝ ሳያየው የማይመለስ ገዳም ነው።
ከቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት 80 ዓመት ቀድሞ የተመሠረተ ነው። በሕንፃ ጥበቡ፣ በግድግዳ ላይ ሥዕሎቹ እና ከእንጨት በተሠሩ ውብ የኾኑ ቅርሶች ይታወቃል። ይህ ገዳም ይምርሃነ ክርስቶስ ይባላል። ይህ ድንቅ ስፍራ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ ነው የተመሠረተው።
ከዋሻ በታች በእንጨት እና በድንጋይ የታነጸ ኾኖ መሠረቱ ውኃ ላይ ያረፈ መኾኑን እና በቀላሉ ሊበሠብሥ ከማይችል “ዞጴ” ተብሎ ከሚጠራ የእንጨት አይነት ተረብርቦ መሠራቱን የቅዱስ ላሊበላ የአስጎብኝዎች ማኅበር አባል አቶ አበበ ደምሳሽ ገልጸውልናል። በሕንፃ ሥራው ወቅት ድንጋዮቹን እና እንጨቶቹን ለማጣበቅ ኖራ መሰል ድንጋይ ለረጅም ጊዜ እንዲበሠብሥ ተደርጎ ከእንቁላል አስኳል ጋር ተቀላቅሎ ጥቅም ላይ መዋሉንም ነግረውናል።
ብዙዎችን የሚያስገርመው ግን መሠረቱ በውኃ ላይ ፀንቶ መቆየቱ ነው። ይህ ከዓለማዊ ጥበብ ባለፈ መለኮታዊ ስጦታም ጭምር መኾኑን የሚናገሩት አስጎብኝው የቤተ ክርስቲያኑ የውስጥ ክፍሎች በውብ የግድግዳ ላይ ሥዕሎች እና በሚያምሩ ከእንጨት የተሠሩ ጌጦች የደመቀ በመኾኑ ብዙ ጊዜ ጎብኝዎች ሀሴትን አድርገው ይመለሳሉ ብለዋል።
ይህ መንፈሳዊ ስፍራ ከላሊበላ ቀጥሎ ውብ ነው ያሉን አቶ አበበ በርካታ ጎብኝዎችም ለማየት የሚመርጡት ቦታ እንደኾነ ገልጸውልናል። የቅዱስ ላሊበላ አቢያተ ክርስቲያን እና የይምርሃነ ክርስቶስ ገዳማት የሥጋ ዝምድና ባላቸው እና ከአራቱ የዛጉዬ ቅዱሳን ነገሥታት ውስጥ ሥማቸው ከፍ ብሎ በሚጠራላቸው የጨለማ ዘመን መብራቶች የተመሠረቱ ናቸው።
ንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ ለንጉሥ ላሊበላ አጎት ናቸው። “አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው” እንዲሉ ንጉሥ ይምርሃነ ለቅዱስ ላሊበላ መንገድ ጠርገዋል። በየዓመቱ የኢየሱስ ክርስቶስን እና የቅዱስ ላሊበላን የልደት በዓል ለማክበር ወደ ላሊበላ ከተማ የሚመጣ ሁሉ እግረ መንገዱን ይምርሃነ ክርስቶስን ጎብኝቶ እና መንፈሳዊ በረከትን አግኝቶ ይሄዳል።
ታኅሣሥ 29 የሚከበረውን የልደት በዓል አስቦ እና በቂ ጊዜ ይዞ የሚመጣ ጎብኝ እግረ መንገዱን በጎበኛቸው የሚያተርፍባቸው በርካታ መዳረሻዎች አሉ። ለዓብነት አሸተ ማርያም፣ ገነተ ማርያም፣ ነአኩቶ ለአብ፣ ብልባለ ጊዮርጊስ፣ ብልባላ ቂርቆስ እና ስርዝና ሚካኤል ተጠቃሽ ናቸው። የሚያምር መልክዓ ምድር፣ ድንቅ የሥዕል ጥበብ እና ድንቅ የኪነ ሕንፃ ጥበብ ጎልቶ የሚታይባቸው መንፈሳዊ ሥፍራዎችም ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!