ከትልቁ ስምጥ ሸለቆ እስከ አፋር በረሃዎች በአንድ በር ቁልቁል የሚያስመለክተው የምኒልክ መስኮት።

0
562

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምኒልክ መስኮት ከአዲስ አበባ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ደብረ ብርሃን ከተማን አልፎ 170 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ቦታ ከደብረ ብርሃን ከተማ ወደ ሰሜን አቅጣጫ በሚወስደው አስፓልት 4ዐ ኪሎ ሜትር ያክል እንደተጓዙ “አንዲት ጥድና ጅብ ዋሻ” የሚባሉ አካባቢዎችን ያገኛሉ፡፡ የምኒልክ መስኮት ወደ ቀኝ በመታጠፍም ወደ ተራራ ሲወጡ የሚያገኙት ተፈጥሮአዊ ክስተት ነው፡፡

ቦታው በጣም ከፍተኛ ተራራ ላይ የሚገኝ በመኾኑ ዓመቱን ሙሉ ለምለም ነው፡፡ አካባቢው በአረንጓዴ ሸማ የተሸፈነ ተፈጥሮ ውበትን ያለበሰችው አስደናቂ ሥፍራ ነው፡፡

መልክዓ ምድሩ ሥራዬ ብለው የሚመጡትን ጎብኚዎች ብቻ ሳይኾን የአልፎ ሂያጁን ቀልብ ይስባል፡፡

“የምኒልክ መስኮት” ወይም “ገማሳ ገደል” በ19ኛው እና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነግሰው የነበሩት ዳግማዊ ምኒልክ አካባቢውን ያዘወትሩት ስለነበር ስያሜውን ከዚያ እገኘው ተብሎ ይታመናል።

አንዳንድ የታሪክ አዋቂዎች ደግሞ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በንግሥና ዘመናቸው ወደ አያታቸው ንጉሥ ሣሕለ ሥላሴ የትውልድ ቦታ ወደኾነችው ሰላድንጋይ ከተማ ለተለያዩ ጉዳዮች ይመላለሱ ነበር፡፡ በተደጋጋሚም በቦታው እየተገኙ ይዝናኑ ነበር፡፡

ታዲያ የአካባቢው ነዋሪዎች የዚህን ሥፍራ መጠሪያ “የምኒልክ መስኮት” የሚል ስያሜ ሰጡት የሚሉ አሉ። እስካኹን ድረስም ሥፍራው በዚሁ ስያሜ እየተጠራ መገኘቱን ድርሳናት ያወሳሉ፡፡

በዚህ ሥፍራ በመገኘትም ትልቁ የስምጥ ሸለቆ የሚያልፍባቸውን አካባቢዎች ይቃኛሉ፤ አካባቢውን ቆም እያሉ በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ይደነቃሉ፤ ይደመሙም እንደነበር የሰሜን ሸዋ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ድርሳን ስለገማሳ ገደል ተፈጥሮአዊ ውበት ያትታል።

ከምኒልክ መስኮት እየፈለቀ ከጥዋት እስከ ማታ የሚጎተተው ጉም መንፈስን ይገዛል፡፡ ነፋሻማ አየሩ ሀሴትን ያጭራል፡፡ ስለኾነም መሰል ትይንቶች የምኒልክ መስኮትን ሁልጊዜ የማይሰለች እና አስደሳች ሥፍራ ያደርጉታል፡፡

በምኒልክ መስኮት በኩል ወደ ምሥራቅ ቁልቁል አሻግረው ሲመለከቱ በተዋጣለት መሐንዲስ ተከርክመው የተሠሩ የሚመስሉ ግራ እና ቀኝ ቀጥ ብለው የሚገኙ ተራራዎችን ከነግርማ ሞገሳቸው ይመለከታሉ፡፡

ይህ አካባቢ ሁል ጊዜ ልምላሜ የማይለየው በመኾኑ ዝንጀሮዎች፣ ሽኮኮዎች እና ገደሉን እንደመጠለያ አድርገው የሚኖሩ በርካታ የአዕዋፍ ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡

ለዚህም ይመስላል በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች ከአካባቢው የማይታጡት፡፡

በዚህ ስፍራ የይፋትን ቆላማ መንደሮች፣ ኢትዮጵያን ለሁለት ከፍሎ የሚያልፈውን ትልቁን ስምጥ ሸለቆ፣ የአፋርን ክልል በርሃማ ቦታዎች እና የአዋሽን ወንዝ በአንድ መስኮት በአግራሞት ለመመልከት ያስችላል፡፡

ይህ የሚኾነው ታዲያ ከገደሉ በር እንደ ደመራ ጭስ እየተጥመለመለ የሚወጣው ነጭ ጉም እና የአካባቢውን ቀዝቃዛ እና መንፈስን አዳሽ አየር እየሳቡ ጭምር ነው ፡፡

ሥፍራው የወፍ ዋሻን ደን ከሥሩ ይዟል፡፡ ብርቅየ እንስሳትን እና በርካታ የአዕዋፍ ዝርያዎችን አቅፎም ይገኛል። ማራኪ እና አስደናቂው ሥፍራ የጎብኝዎችን ቀልብ የመሳብ ኃይል አለው፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here