ፖላንዳውያን ጎብኝዎች በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ኪነ ሕንፃ መደነቃቸውን ተናገሩ።

0
148

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በርግጥ ከወጥ ዓለት የተፈለፈሉ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስ ከበርካታ ምዕተ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን የረገጡ ሁሉ ተደንቀውና ተገርመው ጽፈውለታል። ፖርቹጋላዊ አሳሽ ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ላሊበላን ከጎበኘ በኋላ “ይህን ዕፁብ ድንቅ ሥራ ያየሁትን ሁሉ ነገር ብፅፍ የሚያምነኝ ስለማይኖር በዐይናቸው ሂደው ለሚያዩ ትቼዋለሁ” ነበር ያለው።

በአማራ ክልል የሚገኙት አስደናቂ ጥበብ ያረፈባቸው የላሊበላ መካነ ቅርሶች በየዕለቱ አያሌ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ይጎበኛሉ። በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ደጆች የረገጡ የሀገሬ ሰዎችም ሆኑ የውጭ እንግዶች ዛሬም ቢሆን መደነቃቸው አልቀረም።

ኢዜአ በላሊበላ ተገኝቶ ያነጋገራቸው ፖላንዳውያኑ ፒተር፣ ማጉታዥታና ፖም በቅዱስ ላሊበላ ጉብኝታቸው ተደንቀዋል። ፖላንዳውያኑ ቤተሰቦች በኢትዮጵያውያን እንግዳ አቀባበል እሴቶች፣ ድንቅ ባሕል እና ታሪካዊ ቅርሶች እንደተማረኩ በመጥቀስ፤ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል አመስግነዋል።

በተለይም በላሊበላ ኪነ ሕንጻ ውበት መደመማቻውን ገልፀው፤ ይህን ቅርስ በመመልከታቸው ደስታቸው ወደር እንደሌለውም ይናገራሉ። ኢትዮጵያዊ እንግዳ አክባሪ ሕዝብና ለኑሮ ተስማሚ አየር ፀባይ የተቸራት ሀገር በመሆኗ በመላው ዓለም ያሉ ጎብኚዎች ሁሉ ሊጎበኟት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here