ያልተገለጠው የደልጊ ውበት!

0
185

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደልጊ ከተማ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጣቁሳ ወረዳ በጣና ዳርቻ የምትገኝ ከተማ ናት። አመሠራረቷ በአጼ አምደ ጽዮን በ1320 ዓ.ም እንደኾነ ይነገራል፡፡ ከተማዋ ጣና ሐይቅን መሠረት አድርጋ የተመሠረተች፣ በጣናም ውበትን የተላበሰች ናት።
ለቱሪዝም ምቹ የኾነችው ደልጊ ገና ውበቷ ጎልቶ ያልወጣ ሥፍራ ናት፡፡ ጣና የብዙዎች ሕይዎት የተመሠረተበት ሐይቅ መኾኑ በደልጊ ከተማ ያለው የሰዎች መስተጋብር ማሳያ ነው፡፡

በደልጊ የጣና ክፍል ላይ በደንገል በተሠራች ጀልባቸው ሐይቁን እየገመሱ የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን የሚከውኑት አቶ አብየ ተስፋሁን የደልጊ ከተማ ሕልውና እና የኑሮ መሠረታችን የሐይቁ መኖር ነው ያላሉ፡፡ የደልጊ ከተማን ለመጎብኘት የሚመጡ የሀገር ውስጥም ኾነ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ዓሳ በማቅረብ ከራሳቸው አልፈው ለከተማዋ ትልቅ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙም ነው የሚገልጹት፡፡

በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር እንቅፋት ከመኾኑ አስቀድሞ ዓሳ ለከተማዋ ከማቅረብ አልፈው እስከ ሱዳን ድረስ ይልኩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ደልጊ ገጸ በረከቷ ብዙ ነው የሚሉት አቶ አብየ አካባቢው የቅመማ ቅመም እና የበርበሬ ምርት በስፋት እንደሚመረትበትም ተናግረዋል። ምርቱ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ድረስ የሚላክ ደረጃውን የጠበቀ መኾኑንም ገልጸዋል።

የተፈጠረው የጸጥታ ችግር አካበቢ ከሚመጡ ጎብኝዎች ይገኝ የነበረውን ገቢ አሳጥቷል። ደልጊን እንደ ጎርጎራ ማልማት ይገባል የሚሉት አቶ አብየ የጎርጎራ ውበት በገባታ ለሀገር እንደተገለጠው ሁለ የደልጊ ውበትም ቢገለጥ ምኞቴ እና ፍላጎቴ ነው ብለዋል። የጣቁሳ ወረዳ ባሕል ቱሪዝም የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ፈንቴ እምቢቢል ደልጊ ከራሷ አልፋ ለሀገር የሚበቃ የቱሪዝም ሃብት ያላት ከተማ መኾኗን ተናግረዋል።

ለደልጊ ውበት የጣና ሐይቅ ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የደልጊ ከተማ ዕድገት እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ቡድን መሪው በቱሪዝም ሃብት ሀገር ሊጠቅም የሚችል ሃብት ያላት ናት ብለዋል፡፡ በከተማዋ ያለው ወደብ ለከተማዋ ዕድገት የራሱን አሻራ እንዳሳረፈም ተናግረዋል። ከደልጊ ጎርጎራ እና ባሕርዳር በጀልባ ሽርሽር ለማድረግ አመች የኾነች ስፍራ እንደኾነችም ገልጸዋል።

በከተማዋ መዋለ ንዋያቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ ባለሃብቶችም ካሉ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው አመች ጸጋ እንዳለም አንስተዋል። ደልጊን እንደ ጎርጎራ ውበቷን ለመግለጥ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር እየመከሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ከተማዋ ለቱሪስት መዳረሻ ትኾን ዘንድ እንደ ገበታ ለሀገር ያሉ ፕሮጀክቶች እንደሚያስፈልጓት የሚናገሩት ቡድን መሪው ለከተማዋ ልማት ባለሃብቶችም መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።

በደልጊ የጣና ክፍል የሚመረተው የዓሳ ምርት ከአካባቢው እስከ ሱዳን የሚዘረጋ እንደኾነ ነግረውናል፡፡ እነ ጣናነሽ፣ ሊማሊሞ እና አንድነት የመሳሰሉ ጀልባዎች መዳረሻ መኾኗ ለቱሪስት ምቹ ከተማ እንድትኾን እንዳደረጋትም ገልጸዋል። የአጼ ቴዎድሮስ ምሽግ፣ የአጼ ዮሐንስ ዋሻ፣ የማይ ዋሻ እና ጥንታዊ አብያተክርስቲያናት እና ገደማት በደልጊ እና አከባቢዋ ይገኛሉ።

በአካባቢው ያለው የቱሪዝም ሃብት ከተማዋን ለጎብኚዎች ምቹ እንደሚያደርጋትም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here