በሩብ ዓመቱ ከ6ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች የአማራ ክልልን ጎብኝተዋል።

0
115

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በሩብ ዓመቱ ከ6ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች የአማራ ክልልን መጎብኘታቸውን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል። የአማራ ክልል በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በክልሉ ዓይን ከፋች፣ ተመራጭ የኾኑ፣ ሊጎበኙ የሚገባቸው፣ የዓለምን ቀልብ የሚስቡ የመስህብ ሃብቶች ይገኛሉ።

በክልሉ በተደጋጋሚ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ጎድቶታል። የጸጥታ ችግሩ ጎብኝዎች በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ ሲያደርጋቸው ቆይቷል። ነገር ግን ከጸጥታ ጎን ለጎን የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲጨምር እየተሠራ ነው። ከጸጥታ ጎን ለጎን ጎብዎች ወደ ክልሉ እየመጡ ነው። የጸጥታ ችግሩ ባይኖር ደግሞ የጎብኝዎች ቁጥር ከፍተኛ ይኾን ነበር። ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢም ይጨምር ነበር።

የአማራ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የክልሉን የቱሪዝም ዘርፉ እንዲያድግ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ፍሰት እንዲጨምር እየሠራ ነው። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ4 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ክልሉን ይገበኙታል ተብሎ መታቀዱን አስታውሰዋል።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ6 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች መጎብኘታቸውን ተናግረዋል። ከ2 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ክልሉን ይጎበኙታል ተብሎ ታቅዶ ከ3 ሚሊየን በላይ የሚኾኑ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ወደ ክልሉ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከውጭ ሀገር ጎብኝዎች ከ34 ሚሊየን ብር በላይ ተገኝቷል ነው ያሉት። ከሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ደግሞ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ መገኘቱን አስታውቀዋል።

በሩብ ዓመቱ ከተያዘው ከእቅድ በላይ መሳካቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እና የሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ኹኔታ ዝቅ ማለቱን ነው የገለጹት።

በክልሉ የተከበሩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክብረ በዓላት፣ የባሕርዳር እና የጣና ገደማት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ የስሜን ተራራዎች እና ሌሎች የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን የሳቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች መኾናቸውን አንስተዋል።

የተሠራው የገጽታ ግንባታ፣ የመስህብ ሀብቶች የተዋወቁበት ደረጃ እና በመዳረሻዎች ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ መጠናከር ጎብኝዎችን እንዲስቡ ማስቻሉንም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here