ቱሪስቶች በስፋት ወደ ክልሉ እንዲገቡ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

0
194

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ክልል በቀጣይ በሚከበሩ በዓላት የቱሪስት መዳረሻ እንዲኾን ለማስቻል የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ክልሉ ባለፉት ዓመታት በኮረና ወረርሽኝ፣ በጦርነት እና ግጭት ምክንያት የቱሪስ ፍሰቱ ቀንሶ ቆይቷል፡፡ ይህን የቱሪስት ፍሰት ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ እንዲቻል ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ለአሚኮ ገልጿል፡፡

አማራ ክልል ካለው ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ የቱሪስት መስህቦች ተጠቃሚ እንዲኾን መሥራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም ገልጸዋል፡፡ አሁን ክልሉ ካለው አንጻራዊ ሰላም በመነሳት በወረርሽኙም ኾነ በሰላም እጦቱ ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱረዝም እንቅስቃሴ በማነቃቃት ጎብኝዎች ወደ ክልሉ እንዲመጡ የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እየተሠራ መኾኑንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

በታኅሣሥ ወር መጨረሻ እስከ የካቲት ወር ድረስ በርካታ የቱሪዝም መስህብ ሁነቶች እንደሚካሄዱ የገለጹት ዳይሬክተሩ እነዚህን ሁነቶች ተጠቅሞ ቱሪዝሙን ማነቃቃት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በተለይም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ፣ የጥምቀት በዓል በጎንደር እና በምንጃር፣ የአስተርዮ በዓል በመርጦ ለማርያም እና በደብረ ወርቅ፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል በአዊ ብሔረሰብ፣ የመርቆሪዎስ ዓመታዊ በዓል፣ የግሽ ዓባይ (ሰከላ) ዓመታዊ በዓል ከተያዘው ወር ጀምሮ አስከ የካቲት መጨረሻ ድረስ የሚከበር በመኾኑ ይህን ሁነት በሚገባ መጠቀም እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

በእነዚህ ባዕላቶች ከ4 ሺህ በላይ ቁጥር ያላቸው የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እና ከ2 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች አማራ ክልልን ይጎበኛሉ የሚል ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደኾነም ነው አቶ መልካሙ አዳም ያብራሩት፡፡ ወደ ክልሉ ከሚገባው ቱሪስትም ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ይገኛል ተብሎ መታሰቡንም ነው ዳይሬክተሩ ያስገነዘቡት፡፡

ቢሮው ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመኾን ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡ ቱሪስት ወደ ክልሉ ገብቶ እንዳይጉላላ በየመዳረሻዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ የሀገር ውስጥም ኾነ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ ክልሉ በመምጣት በበዓላቱ እንዲታደሙ እና እንዲጎበኙ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here