ዋግ እና “ብርኩተ “

0
152

ሰቆጣ : ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በበርካታ ባሕሎች የሚታወቅ አካባቢ ነው። ከባሕላዊ ጨዋታዎች ውስጥ ሻደይ፣ ለውፈረ ለውፈ፣ ቕየ ቕየ እና ሌሎች ባሕላዊ ጨዋታዎች ይገኙበታል። የአካባቢው ማኅበረሰብ በዋናነት የ”ኽምጣና” ቋንቋ ተናጋሪ ሲኾን አማርኛ እና ትግረኛም ተናጋሪ ናቸው። ዋግ ኽምራ ባሕላዊ ምግቦች እና መጠጦች ያሏት ሲኾን ከእነዚኽም ውስጥ አንዱ የኾነውን የ”ብርኩተ” ምግብ አሠራር ይጠቀሳል።

“ብርኩተ” በስንዴ ዱቄት ወይም በማሽላ ዱቄት ሊሠራ የሚችል ሲኾን በዋናነት ፍየል በማርባት በርሃ የሚውሉ እረኞች ዘንድ የሚዘወተር የምግብ ዓይነት ነው። እረኞች በርሃ ስለሚውሉ እሳት ለማንደድ የዘመኑን ክብሪት የማግኘት ዕድላቸው ጠባብ ነበር። እናም እንጨት በእንጨት በማጋጨት እሳት የመፍጠር ዘዴን ይከውናሉ።

“ባዝቓ፣ እንቋ፣ ውጭነ..” የተባሉ በአካባቢው የሚጠሩ እንጨቶችን እርስ በእርስ በመቦርቦር ወይም በአካባቢው አጠራር “ጭረ፣ ጭረነ፣ ጃቕለ” ይሉታል ፤ እነዚህን እንጨቶች እርስ በእርስ በመፈተግ እሳት ይፈጥራሉ። ቶሎ አመድ የማይኾኑ እና ፍም መጣል የሚችሉ እንጨቶችን በመጠቀም እሳቱ እንዲደምቅ ይደረጋል። በአካባቢው አጠራር “ሽፈልሻ፣ ጻሎ፣ እክመ፣ አቭረት ቃነ” ወዘተ የተባሉ እንጨቶች የበለጠ “ብርኩተ” ለመጋገር ተመራጭ ናቸው።

ከወንዝ የተመረጠ እና የማይሰነጠቅ፣ የማይሰበር ክብ ድንጋ በማምጣት ከሚነደው እሳት ላይ በማስገባት እንዲግል ያደርጋሉ። ድንጋው እስኪግል ደግሞ በተጓዳኝ የያዙትን የስንዴ ዱቄት “ብልባል” በተባለ ቆዳ ላይ ዱቄቱን በውኃ ያቦኩታል ወይም በመጠኑ ያዋህዱታል። በመቀጠልም የተዋሃደውን ሊጥ ከፍሙ ካለው የጋለ ድንጋይ ላይ ዙርያው እስኪከደን ድረስ በሊጡ ይሸፍኑታል። የጋለው ድንጋይ ሙሉ በሙሉ መከደኑን ሲያረጋግጡ መልሰው ወደ ፍሙ ያስገቡታል። መብሰሉን ሲያረጋግጡ ክቡን ድንጋይ ከፍም እሳቱ ያወጡታል።

በዚህ መንገድ እንደ ሰው መጠን ጨማምረው ያስገባሉ። በዚህ ዓይነት የተጋገረውን የክብ ድንጋይ ምግብ”ብርኩተ” እያሉ ይጠሩታል። መብሰሉን ሲያረጋግጡ አውጥተው ከሁለት ገምሰው ድንጋዩን ለሌላ ቀን መጋገሪያ በመተው የበሰለውን “ብርኩተ” እንዲቀዘቅዝ ከንጹህ ድንጋይ ወይም ፍልጥ እንጨት ላይ ይደረድራሉ። የበረደውን “ብርኩተ” እረኞቹ በጋራ በመኾን” በቅል ወተት” እያማጉ ይጠቀሙታል።

“ብርኩተ በወተት አምጎ ያደገው”
“ባቱ ደንዳና ነው ያስታውቃል ከኋላው”

የተባለለት የብርኩተ ምግብ አሠራር እስከ ዛሬ ድረስ በግ እና ፍየል በማርባት የተሰማሩ ወጣቶች ዘንድ የሚዘወተር እና ተወዳጅ ምግብ ነው። 21ኛውን የመላው ዋግ ኽምራ ባሕል እና ስፖርት 6ኛውን የባሕል ፌስታባል ያዘጋጀው የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ለባሕል ስፖርት ተወዳዳሪዎች የ”ብርኩተ” ምግብ አሠራርን በተግባር አሳይተዋል። ባሕል እና ወግ የአንድ ማኅበረሰብ ማንነት መገለጫ ነው።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here