“ሰማይን የመሰለች፤ በጥበብ የታነጸች”

0
148

ወልድያ: ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በልቦና የምትታሰበውን፣ ተስፋም የምትደረገውን የቅዱሳኑን ማደሪያ፣ የጻድቃኑን መኖሪያ ረቂቋን ሰማይን ትመስላለች ይሏታል። በምድር ከተሠሩት ረቂቅ ጥበቦች ሁሉ ትለያለች። ከዓለም ጥበብ ሁሉ ትልቃለች። ከምድር ጥበባት ሁሉ ከፍ ብላ እጹብ ድንቅ ትሰኛለች ትባላለች።

በመጽሐፍ የተጻፈው በዓለት ላይ ተቀርጾባታል። በልብ የሚታሰበው በረቀቀ ጥበብ ይታይባታል። ዓለት እንደ ግራምጣ ተሰንጥቆባታል። ለቅዱሳን እጆች ታዝዞባታል። ባማረ ውበት ታንጾባታል። ጻድቃን ያበጃጇት፣ በቅድስና የሚኖሩባት፣ ብጹዓን የሚመላለሱባት፣ በሰርክ ጸሎት የሚደረስባት፣ ምሥጋና እና ውዳሴ የማይለይባት፣ ምልጃ የማይታጓጎልባት፣ የጽድቅ ሥራ የማይጠፋባት ቅድስት ሥፍራ ናት።

ቅዱሳት መጻሕፍት የመዘገቡት፣ ቅዱሳን ስዕላት የሚናገሩት በዓለት ላይ ይነበብባታል። ሰማያዊት እና ምድራዊት ኢየሩሳሌም ይገለጡባታል። በረከት ያለ ማቋረጥ ይረብባታል። ረድኤት ሰፍኖ ይኖርባታል። በረከትን የሚሹ፣ ረድኤትን የሚፈልጉ ሁሉ ይሰባሰቡባታል። በአንድነትም ይጸልዩባታል። በኅብረት ለአምላካቸው ምልጃ ያቀርቡባታል ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም።

ደብረ ሮሐ ኢትዮጵያ የምታጌጥባት፣ በዓለሙ ፊት ሁሉ ደምቃ የምትኖርባት፣ ቅዱሱ እና ንጉሡ ያዘጋጇት፣ አምላክ ለልጆቹ ጥበብን የገለጠባት፣ ለትወልድ ሁሉ መኩሪያ እና መመኪያ ትኾን ዘንድ የሰጣት፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ደምቀው የሚታዩባት፣ ረቂቅነታቸውን የሚገልጹባት ረቂቅ ሥፍራ ናት። ከውቅያኖስ ላይ ለጥም ያክል ጥቂት ይጠጣል። ከፀሐይ ብርሃን ለሙቀት ያክል ጥቂት ይሞቃል እንጂ ውቅያኖስን ማን ጨልፎ ይጨርሳል። የፀሐይን ሙቀትስ ሙሉውን ማን ይቋቋማል። የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላም ዝም ከማለት ጥቂት ይጻፋል እንጂ ሙሉን ማን ጽፎ ይጨርሳል?

የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አሥተዳዳሪ አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ ይህች ሥፍራ አበው የሰጡን፣ አምላክም እንድትገለጥ የፈቀዳት ረቂቅ ሥፍራ ናት ይሏታል። ቅዱስ ላሊበላ የረቀቁ አብያተ ክርስቲያናትን ከማነጹ አስቀድሞ ኢትዮጵያውያን በዓለ ልደትን ለማክበር ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ወደ ቤተልሔም ያቀኑ ነበር። ዘመኑም እንደዛሬው በአየር መብረር ያልነበረበት ነበርና እኒያ ለበረከት የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ፈተናው ይበዛባቸው፤ መከራው ይጸናባቸው ነበር ነው የሚሉት።

ይህም ኾኖ በረከትን የሚሹ ኢትዮጵያውያን በዓለ ልደትን ለማክበር ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ወደ ቤተልሔም ያቀኑ ነበር። በቤተልሔም በደረሱ ጊዜም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በግርግም የተወለደበትን አይተው ተደንቀው፣ ጸልየው፣ አምልኳቸውንም ፈጽመው ይመለሱ ነበር። ንጉሡ እና ቅዱሱ ላሊበላም የንግሥና ዘውዱን ከመጫናቸው አስቀድመው ገና በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው በዓለ ልደትን በቤተልሔም አክብረው ነበር ይላሉ። በዚያም በዓለ ልደትን ካከበሩ በኋላ ስለ ሁለት ነገር አብያተክርስቲያናትን ያንጹ ዘንድ ፈቃድ ኾነ።

ቅዱስ ላሊበላ ወደ ሰማይ ተነጥቀው በሰማይያለውን ምስጢር አዩ። የከበረውን ነገር ተመለከቱ። ከዚያም በኋላ ላመኑ እና እግዚአብሔርን ተስፋ ለሚያደርጉ በዚህች ድንቅ ምድር በሰማይ ያለውን ምስጢር የሚያዩበት፣ የሚዳስሱት፣ የሚነኩት ድንቅ ነገርን ለመሥራት የእግዚአብሔር መንፈስ አነሳሳቸው። በሌላ በኩልም በረሃውን አቋርጠው በዓለ ልደትን እና በዓለ ትንሳኤን ለማክበር የሚሄዱ ሰዎች የሚያርፉበትን፣ አምላካቸውን የሚያመልኩበትን ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን አስመስለው እንዲያንጹ የእግዚአብሔር መንፈስ አነሳሳቸው ይላሉ።

አብያተ መቅደሳቱ ብሉያትን እና ሐዲሳትን ያሰናሰሉ፣ አማኞች አንብበው ከማየት ባሻገር አይተው ዳስሰው እንዲረዱ የሚያደርጉ ረቂቆች ናቸው ይሏቸዋል፤ ስለ ምን ቢሉ በመጻሕፍት የተጻፉት በዓለት ላይ ተቀርጸዋልና። በዚህ ዓለም ያሉ መሐንዲሶች እና ቤት ሠሪዎች፣ በስዕል ተስሎ፣ በዲዛይን ተዘጋጅቶ የተሰጣቸው ነገር እየተበላሸባቸው ሲያፈርሱ ሲሠሩ ይኖራሉ። ቅዱስ ላሊበላ ግን በየትኛውም ዘመን የማይሠራ ዓለምን ያስደመመ እጹብ ድንቅ ሥራ ሠሩ ተብሎ በገድላቸው ተጽፏል።

እጹብ ድንቅ ኾነው፣ በአንድ ንጣፍ ዓለት ድንጋይ ላይ በልበ ምድር ተፈልፍለው የተሠሩት አብያተክርስቲያናት በሥነ ጥበብ ይዘታቸው፣ በአሠራር ጥራታቸው እና ዐይንን በሚስብ ውበታቸው ሥልጣኔ በኢትዮጵያ ምን ያክል እንደ ፀሐይ አብርቶ፣ የቱንስ ያክል የኪነ ጥበብ አበባ ፈክቶ እንደነበር የሚያዘክሩ ምስክሮች ናቸውም ተብሎ በገድላቸው ተመዝግቧል።

በገድለ በቅዱስ ላሊበላ “የእነዚህን አብያተክርስቲያናት ሥራ መናገር በምን አንደበት መናገር እንችላለን? የውስጣቸውንስ እንተውና የቅጽራቸውን ሥራ እንኳ መናገር አንችልም። ያየም በማየት አይጠግብም። ልቡ አርፎ ከማድነቅ ቼል አይልም። ታሪኩን ይቆጥር ዘንድ ለሰው የማይቻለው በላሊበላ ድንቅ የኾነ ታሪክ ተሠርቷልና። በላሊበላ እጅ የተሠሩትን አብያተክርስቲያናት ሕንጻ ሥራ ያይ ዘንድ የሚወድ ሰው ቢኖር ይምጣ በዐይኖቹም ይይ” ተብሎ ተጽፏል።

የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ለግድግዳቸው እንጨት፣ ለመሠረታቸው ጭቃ፣ ለጣሪያቸው ባጥ እንጨት እና የገመድ ትት፣ ለክዳናቸውም የሰንበሌጥ ሳር የላቸውም። በአንድ ዓለት ላይ ከጣሪያቸው ላይ ተፈጽመው ተጀመሩ። የዓለሙን ጥበብ ሁሉ በናቀ ጥበብ ተሠሩ እንጂ። ኢትዮጵያዊ ኾኖ ካንዲት ድንጋይ የተሠሩትን የእነዚህን አብያተክርስቲያናት ዜና ሰምቶ ቅድስት ወደኾነችው ወደ ሮሐ ያልደረሰና ይህን ያላየ የኢየሱስ ክርስቶስን ፊት ያይ ዘንድ የማይወድ ሰው ይመስላል ተብሎም በገድላቸው ተጽፏል።

ገድላቸው ላይ እንዲህ የሚል መልዕክት አለ “መጥተው ይዩት፣ ያድንቁት፣ ይወቁት። ሺህ ጊዜ ከመስማት አንድ ጊዜ ማየት ይበልጣልና። አይተው ያጥኑት። ሞት እና የላሊበላ ሕንጻ ሁልጊዜ አዲስ ናቸው”

አዎ ደብረ ሮሐ ዘውትር የምትናፈቅ ረቂቅ እና ድንቅ ናት። እዩዋት ተመልከቷት። የኢትዮጵያን ጥንታዊት፣ የኢትዮጵያውያንንም ታላቅነት ታደንቁባታላችሁ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here