“ቃል ኪዳን የሚያኖራት፤ ምርቃት የሚያከብራት”

0
134

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በቃል ኪዳን ይኖራሉ። በበረከት ይውላሉ። በረድኤት ያድራሉ። መልካሙን ነገር ያደርጋሉ። የአበውን ቃል ያከብራሉ። ሥርዓትን ይጠብቃሉ። በቃልና በሥርዓትም ይጠበቃሉ። ምድሯ የአበው ቃል ኪዳን ይረብባታል። ምልጃ እና ጸሎታቸው ይጠብቃታል። ምርቃትም ያከብራታል። ከፍ ከፍም ያደርጋታል። ደጋጎቹ ዝቅ ብለው እግር አጥበው፣ ጉልበት ስመው፣ መንገድ ጠቁመው፣ ለደከመ ምርኩዝ ኾነው፣ የተራበን አጉርሰው፣ የታረዘን አልብሰው፣ የሄደን ስንቅ አስቋጥረው በናፍቆት ሸኝተው ይመረቃሉ። በረከትን ይቀበላሉ። ረድኤትን ወደ ቤታቸው ያስገባሉ።

የመጣ የሄደው ይመርቃቸዋል። እናንተ የደጋጎቹ ልጆች ለዘላለም ክፉ አይንካችሁ። ሰላም እና ተድላ አይለያችሁ። መከራ ይራቃችሁ። ፍቅር እና ደስታ ይብዛላችሁ። ሞገሱ አይራቃችሁ። የምትሰጡት አያሣጣችሁ ይላቸዋል። እነርሱም ምርቃቱን በትህት እና ዝቅ ብለው ይቀበላሉ። በምርቃት በረከትን ያገኛሉ።

በዚያች ምድር ምርቃት ሃብት ናት። ትህትናም ከእንቁ የላቀች ገንዘብ ናት። የቅዱሳኑ ነገሥታት ግርማ አይርቃትም። ቃል ኪዳናቸው አይለያትም። የቅድስ እና ካባቸው ያለብሳታል። የቅድስና ዘውዳቸው ሞገስ ይኾናታል። የቅድስና በትራቸው ባሕሩን እየከፈለ ያሻግራታል። የቅድስና ዙፋናቸው በክብር ያሳያታል። የቅድስና ጸጋቸው ጸጋውን ያበዛላታል። የረቀቀች ጥበባቸው ከዓለሙ ሁሉ በጥበብ ይለያታል። ሕዝብ ሁሉ እንዲወዳት አድርጓታል ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ።

በቅዱሳን ነገሥታት ቃል ኪዳን የሚተማመኑት፣ ሥርዓታቸውንና ትውፊታቸውን የሚጠብቁት፣ የትናንቱን ከእነ ክብሩ ያኖሩት፣ ከእነ ቅድስናው ያቆዩት፣ የአበውን ምክርና ተግሳጽ የሚሰሙት የላሊበላ ልጆች አኗኗራቸው ይደንቃል። ትህትናቸው ያስደምማል። ሰው ወዳድነታቸው፣ እንግዳ ተቀባይነታቸው፣ ሥርዓት አክባሪነታቸው፣ ትውፊትና ባሕል ጠባቂነታቸው አጀብ ያሰኛል። ከጠዋት እስከ ማታ እንግዳ እየተቀበሉ ደከመን አያውቁም። ከጠዋት እስከ ማታ እግር እያጠቡ አይሰለቹም። ይልቅስ ከፊታቸው ላይ የደስታና የደግነት ፈገግታ ደምቃ ትታያለች እንጂ።

ይሄን ሁሉ ስለ ምን ታደርጉታላችሁ? ተብለው በተጠየቁ ጊዜ ከልብ የመነጨችውን ምርቃት፣ በሰማይ ክብር የምታሰጠውን በረከት እና ረድኤት ለማግኘት ነው። ከእነዚህ የላቁ ሃብቶች ከየት ይገኛሉ? ብለው ይመልሳሉ። የድካም ዋጋቸው ምርቃት እና በረከት ነውና። ኢትዮጵያ የሰው ዘር መጸነሻ፣ የሥልጣኔ መነሻ ማዕከል፣ የእውነተኞች ምድር፣ የነጻነት ባለቤት፣ የታሪክ መዝገብ፣ የቅርስ መደብር፣ የውርስ መዘክር ፣ የባሕል እምብርት፣ የቋንቋና የፊደል እትብት እየተባለች ትጠራለች። ዓለም በጨለማ በተከበበት፣ ብዙዎችም ከእንቅልፋቸው ባልነቁበት ዘመን ኢትዮጵያ አግራሞት እና አድናቆት የሚቸራቸው ብርቅና ድንቅ የጥበብ ሥራዎችን የሠራች የዘመን እና የጥበብ ማከማቻ የኾኑ ቅርሶችን ያበረከተች ድንቅ ሀገር እንደኾነች ይነገርላታል።

ድንቅነቷን ከሚገልጡላት፣ ረቂቅነቷን ከሚያሳዩላት ድንቅ ሃብቶች ደግሞ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ከፊት የሚሰለፉት ናቸው። በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰባሰቡት፣ በጋራና በአንድነት የሚጸልዩት ደጋጎቹ ደግሞ ኢትዮጵያ የደጎች፣ የመልካሞች፣ የእንግዳ ተቀባዮች፣ የሰው ወዳዶች ሀገር እንደኾነች ይመሰክራሉ።

በገድለ ቅዱስ ላሊበላ ( ገብረ መስቀል) ” በዚህ በተሰባሰብንበት፣ ለሁላችን ተስፋ ይሁነን። የጸሎቱ ኀይል ለራሳችን መመኪያ የራስ ወርቅ እንዲኾነን፣ ለፊታችንም ብርሃን ይሁነን። ለዐይኖቻችን የሚያድን ኩል፣ ለጆሯችን የምሕረት ጉትቻ ይሁነን። ለአፍንጫዎቻችንም በጎ መዓዛ ይሁነን። ለከንፈሮቻችንም እውነተኛ ማኅተም ይሁነን። ለጫንቃችንም የሚያስደስት መጎናጸፊያ ይሁነን። ለደረታችንም ድል መንሻ ጋሻ ይሁነን። ለእጆቻችንም የምሕረት አምባር ለጣቶቻችንም የፍቅር ቀለበት ይሁነን። ለእግሮቻችንም ከሾህ ከእንቅፋት የምንድንበት ጫማ ይሁነን። ስንራብ ከረሃብ የምንድንበት እንጀራ፣ በተጠማንም ጊዜ የሕይወት መጠጥ ይሁነን። ወደ ገባበትም ሠርግ ቤት መንግሥተ ሠማያት ከእርሱ ጋር ያግባን” ተብሎ እንደተጻፈ በስሙ በተሰየመች፣ በስሙና በክብሩም በምትኖር ከተማ የሚኖሩ ደጋጎች በቃል ኪዳኑ ይኖራሉ።

ችግርም ቢመጣ፣ መከራም ቢበዛ በልበ ሙሉነት በእርሱ ቃል ኪዳን እንኖራለን። ምግባችንና መጠጣችን፣ ልብሳችንና ጌጣችን፣ ሰላምና ደስታችን እርሱ ነው ይላሉ። አዎን እነርሱ አዝመራቸው ላሊበላ ነው። የማያልቅ ሕብስት ሰጥቷቸዋልና ድንቁን ሥራ ሊያዩ ከሚመጡ ጎብኝዎች የዓመት ልብሳቸውን፣ የዕለት ጉርሳቸውን ያገኛሉ።

አዎን ላሊበላ ጌጣቸው፣ ሃብታቸው፣ መታወቂያቸው ነው። መጠለያ ዋሻቸው ነው። መሻገሪያ ድልድያቸው ነው። አዎን ላሊበላ ከተማ ቃል ኪዳን የሚያኖራት፣ ምርቃት የሚያከብራት ናት። በረከቱ አራቀባትም።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here