ባሕር ዳር: ጥር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 16ኛው የአማራ ክልል ባሕል እና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ከጥር 07/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 09/2017 ዓ.ም በጎንደር ከተማ እንደሚካሄድ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ አስታውቀዋል፡፡
ፌስቲቫሉ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ ባሕል እና ቋንቋን ለማንፀባረቅ እንዲሁም የዕደ ጥበብ እና የኪነ ጥበብ እንቅስቃሴዎችን ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
በተለይም የዕደ ጥበብ ውጤቶች የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጉልቶ በማሳየት በኩል ውስንነቶች መኖራቸውን የገለጹት ኀላፊው ይህ ፌስቲቫል ለእነዚህ ሥራዎች ዕውቅና የሚሰጥ ይኾናል ብለዋል።
ፌስቲቫሉ የባሕል እና የኪነ ጥበብ መድረኮችን ማዘጋጀት መቻሉ የገበያ እድሎችን ለማስፋት እና ጀማሪ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ለማበረታታት የራሱን አወንታዊ ሚና ይወጣል። በፌስቲቫሉ የባሕል እና የኪነ ጥበብ ቡድኖች፣ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የባሕል ሕክምና ባለሙያዎች፣ የቅርጻ ቅርጽ እና የሥነ ስዕል ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡
በፌስቲቫሉ ሙዚቃ፣ ቴአትር፣ ውዝዋዜ፣ የባሕል አልባሳት ፋሽን ትርኢት ይደረጋል፤ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ስዕሎች እና ቅርጻ ቅርጾች ለገበያ ይቀርባሉም ብለዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!