ባሕር ዳር: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምስጢር ይመነጭበታል፣ የጥንት ታሪክ ይነገርበታል፣ ቀደምትነት ይገለጥበታል፤ ሥልጣኔ ይታወጅበታል፣ ረቂቅነት ይመሰከርበታል፡፡ ሃይማኖት ይሰበክበታል፤ እሴት ይገለጽበታል፣ ባሕል ይንጸባረቅበታል፤ ታላቅነት ለዓለሙ ሁሉ ከፍ ብሎ ይታይበታል፡፡
ሥልጣኔ እንደ ፀሐይ በርቶበታል፣ ታሪክ ፈስሶበታል፡፡ ዕውቀት መንጭቶበታል፡፡ እርሱ ከተመረጡት ተመርጧል፡፡ የሚታይ ኾኖ ሳለ የማትታየውን ዓለም ያጠጣል፡፡ በውቧ ሥፍራ ይፈስሳል፡፡ በፈጣሪው ትዕዛዝ ይመላለሳል፡፡ የተመረጠው አፍላግ የፈለቀባት፣ ምስጢራዊ ሐይቅ ያረፈባት፣ የጥፋት ዘመን የተቋጨባት፣ የቃል ኪዳኗ መርከብ ያረፈችባት፣ የዓለም ዕውቀቶች ተጉዘው ያልደረሱባት፣ ታሪክ ያደነቃት፣ ሃይማኖት የጠበቃት፣ ነጻነት የተሰጣት፣ ታላቅነት ባሕሪዋ የኾነላት ምድርም ረቂቅ ናት፡፡
ብርቱ ክንድ የሚጠብቃት፣ የማያንቀላፋው የማይተዋት፣ ቅዱሳኑ የሚመላለሱባት፣ ባሕታውያኑ በጸሎት የሚበረቱባት፣ ምስጢር የሚያትሙባት ምድር ናት፡፡ ብዙዎች ዐይናቸውን ጥለውባታል፡፡ በጠላትነትም ተነስተውባታል፡፡ ጦርም አዝምተውባታል፡፡ ብዙዎችም ምድሯን ለማየት፣ ረቂቅነቷን ለመረዳት ተመላልሰውባታል፡፡
በሸንተረሮቿ ወርደው፣ በታራራዎቿ ወጥተው፣ በሜዳዎቿ፣ በዋሻዎቿ፣ በወንዞቿ ተመላልሰው አጀብ ብለው አድንቀዋታል፤ ታላቋን እና ቀደምቷን ኢትዮጵያን፡፡ ከሩቅ ኾነው አዩዋት ተመለከቷት፣ ሀገራቸውም እንደኾነች አረጋገጡ፡፡ እናም እርሷ ቦታ ገነት ናት፡፡ የገነት ምንጭ በውስጧ ይፈልቃል፡፡
የሕይወት ምንጭ ከእርሷ ይፈልቃል፡፡ እርሷ ገነት ናት የገነት ምንጭም አለባት እንዳለ ሊቁ እርሷ ከተመረጡት የተመረጠው፣ ከተወደዱት የተወደደው አፍላግ የሚፈልቅባት፣ ምስጢር የበዛባት፣ ቃል ኪዳን የታተመባት ናት፡፡ ሥርዓት የጸናባት፣ በሌሎች ዓለማት ሁሉ የሌሉት የሚኖሩባት፣ ዓይኖች ሁሉ በስስት የሚመለከቷት፣ ቅዱስ መንፈስ በላይዋ ላይ የማይጠፋባት ድንቅ ምድር ናት፡፡
“የአፍላጋት መመንጫ የብዙኃኑ እናት አትጠራጠሩ ኢትዮጵያ ምስጢር ናት” እርሷ ገነትን እንደሚያጠጣ የሚነገርለት አፍላግ የሚመነጭባት፣ ብዙኀኑ እናታችን የሚሏት፣ ነጻነት የራባቸው የነጻነት ሕብስት የጠገቡባት፣ በጨለማ የነበሩ ብርሃንን ያዩባት፣ የምስጢር ማሕተም ያለባት ኢትዮጵያ ምስጢር ናት፡፡
ʺእግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ ኤደን ገነትን ተከለ፡፡ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፣ ለመብላትም መልካም የኾነውን ዛፍ ኹሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፣ መልካምን እና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ።
ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከኤደን ይወጣ ነበር፡፡ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር። የአንደኛው ወንዝ ስም ኤፌሶን ነው፤ እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል፤ የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፤ ከዚያም ሉልና የከበረ ድንጋይ ይገኛል። የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ኹሉ ይከብባል። የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፤ እርሱም በስተምሥራቅ የሚሄድ ነው።
አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው። እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በኤደን ገነት አኖረው” እንዳለ መጽሐፍ ግዮን ከኤደን የሚመነጭ፣ ገነትን የሚያጠጣ፣ መስጢር የሞላበት፣ ጥበብ የሚፈስስበት፣ ሥልጣኔ የሚበራበት፣ ቀደምትነት የሚነገርበት ታላቅ አፍላግ ነው፡፡
እርሱ ቅዱሳት መጻሕፍት የመዘገቡት፣ የታሪክ መጻሕፍት የሚናገሩለት፣ ሀገር አሳሾች፣ መነሻውን ያውቁ ዘንድ የሚመላለሱበት፣ ባሕር ሠንጥቀው፣ የብስ አቋርጠው የሚገሰግሱበት ረቂቅ አፍላግ ነው፡፡
ይህን አፍላግ ያፈለቀች ሀገር ደግሞ የተመረጠች ናት፡፡ ይሄን ያኖረች ምድርም የተከበረች ናት፡፡ ምስጢራት የታተሙባት ኢትዮጵያ ምስጢር ናት፡፡ ጥበባት የሞሉባት ኢትዮጵያ ረቂቅ ናት፡፡ የረቀቁት ስጦታዎች ሁሉ የተቸሯት ኢትዮጵያ እጹብ ናት፡፡ ምሥጋና እና ውዳሴ የማይለያት ኢትዮጵያ የተለየች ናት፡፡ የአምላክ ስም ሳይጠራባት የማይውልባት ኢትዮጵያ የበረከት ሀገር ናት፡፡
ግዮን ማለት የሚያስፈራ፣ ትልቅ ነጎድጓድ የመሠለ ድምጸት ያለው ነው ይላሉ አበው፡፡ ግዮን የወንዙን ታላቅነት የሚያስፈራውን ድምጽ፣ ያለውን ግርማ ሞገስ የሚገልጽ ስም ነውም ይሉታል፡፡ “ዐቢይ ወግሩም” ታላቅ እና የሚያስገርም ታላቅ ወንዝ ነው ግዮን ይላሉ ስለ ስሙ ሲናገሩ፡፡
የግዮን ስም አንድ ብቻ እንዳልኾነ እና በቀደሙ ኢትዮጵያዊያን አባዊ ተብሎ እንደሚጠራ ይነገራል፡፡ ይህም የወንዞች ኹሉ ታላቅ፣ ፊትአውራሪ ማለት ነው ይላሉ፡፡ ዓባይ የዛሬም መጠሪያው ነው፡፡
ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን ታሪክ ዘደብረ መዊእ ማርያም ገዳም በተሰኘው መጽሐፋቸው ስለ ዓባይ ሲጽፉ “ ከጥንት ጀምሮ በዙሪያው ይነገሩ በነበሩ ቋንቋዎች አባዊ ይባል ነበር፡፡ አባት ማለት ነው፡፡ ሕይወታቸው ከዓባይ እና ጣና ጋር የተቆራኘው ነጋዴዎች ደግሞ አቢናዝ እያሉ በየዓመቱ የቅበላ ሰሞን በዓባይ ራስ ዓመታዊ በዓል ያከብሩበታል፡፡
በግዕዙ ቋንቋ አብ ከሚለው ሥርወ ቃል በመነሳት አባ፣ አባት፣ አባዊ ይላል፡፡ ያው አባት ማለት ስለኾነ የወንዞች አባት ዋና ጠቅላያቸው እንደማለት ነው፡፡ ብዙ መጻሕፍት ላይ ተጽፎ የምናገኘው ግን በዓይኑ “ዐ” በሚጻፈው ዓባይ ተብሎ ነው፡፡ ይህም “ዐብዬ” ከፍ አለ፣ አደገ፣ ላቀ፣ ገነነ የሚል ፍቺ አለው፡፡ በዚህ መሠረት “ዐባይ” ብለን ወንዙን ስንጠራው ታላቅ፣ ገናና፣ የወንዞች አውራ እንደ ማለት ነው” ብለው ጽፈዋል፡፡
ከገነት አፍላጋት አንዱ የኾነው “ዐባይ” የቅዱሳንን ሕይዎት የሚያለመልም የሕይዎት ምንጭ ፣ የተባረከ ወንዝ ነው ብለውም ከትበዋል ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን፡፡ ይህ አፍላግ ከጎጃም ምድር ከግሽ ተራራ ሥር ከምድር በር ይወጣል፡፡ ሥፍራውም ፈለገ ግዮን እየተባለ ይጠራል፡፡ ይህም ማለት የግዮን መመንጫ ማለት ነው ይላሉ አበው፡፡ ገነትን የሚያጠጣው ግዮን ከግሽ ተራራ ግርጌ ከምድር በር ወጥቶ ረጅሙን መንገድ ይጓዛል፡፡
ከግሽ ተራራ ግርጌ በተከፈተለት የምድር በር ወጥቶ ግርማ ለብሶ ጉዞ የሚጀምረው ግዮን በምስጢራዊው ሐይቅ በጣና ላይ በማለፍ በግራ እና በቀኝ ሌሎች ወንዞችን እያስገበረ፣ መኳንንት እና መሳፍንት፣ የጦር አበጋዞች እና የእልፍኝ አስከልካዮችን በፊት፣ በኋላ፣ በቀኝ እና በግራ እንደሚያጅቡት ንጉሥ በወንዞች እየታጀበ፣ ጉልበቱን እየጨመረ፣ ውኃ ወደተራበበት፣ በረሃ ወደ ጠናበት ምድር ይጓዛል፡፡ ለዚያ ምድርም ሲሳይ ይኾናል፡፡
ግዮን ከምድር በር በሚወጣበት በዚያ ሥፍራ አቡነ ዘርዓ ብሩክ የሚባሉ ጻድቅ ሰው ይኖሩ ነበር፡፡ እኒህ ሰው ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ፣ ሕግጋትን የሚያከብሩ፣ በጾም እና በጸሎት የሚተጉ ጻድቅ ናቸው፡፡ በሠርክ አምላካቸውን ያወድሳሉ፡፡ ስጋቸውን እያደከሙ ነፍሳቸውን ያበረታሉ፡፡ እኒህ ጻዲቅ አባት በረከት የበዛላቸው ነበሩ፡፡
ታዲያ በዘመናቸው ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ በእርሳቸው ዘመን የነገሡ ንጉሠ እስር ቤት ያስገቧቸው ዘንድ ወደዱ፡፡ ወደ ንጉሡ ዘንድ የሚወስዷቸውም ጭፍሮችን ላኩባቸው፡፡ እርሳቸው ዓባይ ከምድር በር ከሚወጣበት ሥፍራ ሲኖሩ ስብሐተ እግዚአብሔር የሚያደርሱባቸው መጻሕፍት ነበሯቸው፡፡
ጻድቁም የንጉሡ ጭፍሮች ሊወስዷቸው በመጡ ጊዜ መጻሕፍቱን የት ላስቀምጣቸው ብለው አሰቡ፡፡ በአጠገባቸውም ከምድር በር ከሚወጣው ከታላቁ ግዮን በስተቀር የሚያምኑት አልነበረም፡፡ ለእርሱም አደራ ይሰጡት ዘንድ ወደዱ፡፡
እነዚያን ቅዱሳት መጻሕት ለግዮን ወንዝ አደራ ሰጡት፡፡ መጻሕፍትን ለውኃ መስጠት እንደምን ያለ ድንቅ ነገር ነው? እንደ ምን ያለስ ምስጢር ነው? ለዓመታት በእስር ላይ ቆዩ፡፡ ከእስር የመለቀቂያቸው ዘመንም ደረሰች፡፡ ወደ ግዮንም መጡ፡፡ በመጡም ጊዜ ስብሐተ እግዚአብሔር አድርሰው ʺግዮን ኾይ መጻሕፍቴን መልስ” አሉት፡፡ ግዮንም መጻሕፍቱን መለሰላቸው ይላሉ አበው፡፡ መጻሕፍቱም ውኃ አልነካቸውም ነበር፡፡ ግዮን ታማኝ፣ ረቂቅ ምስጢር ያለበት፣ ውኃ ብቻ ሳይኾን ቅዱስ መንፈስ የሰፈረበት ነው ይባላል፡፡
አደራ መልሷል፣ ፍቅር እና ክብርን አልብሷልና፡፡ ግዮን ውኃ ብቻ አይደለም፡፡ ከውኃነትም ይሻገራል፡፡ ግዮን ከወንዝነትም ያልፋል፡፡ በዚህ ታላቅ አፍላግ መፍለቂያ በጥር 13 ታላቅ በዓል ይከበራል፡፡ ለግዮን አደራ ሰጥተው፣ አደራውን የተቀበሉት የጻድቁ አቡነ ዘርዓብሩክ ዓመታዊ ክብረ በዓል ይከበራል፡፡ ይህ በዓል ታላቅ እና ደማቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች በዚያች ቅድስት ቤተክርስቲያን ለመባረክ በስፋት ይገሰግሳሉ፡፡
በዚያች ያለችው ጸበልም ፈዋሽ እንደኾነች ያምናሉ፡፡ ከሩቅም ከቅርብ ያሉ ጎብኝዎች ደግሞ የዓለማችን የረጅሙን ወንዝ መነሻ፣ ገነትን የሚያጠጣውን ወንዝ መጸነሻ ለማየት ይጓዛሉ፡፡ በዚህ በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ የጥንቱ እና ያልተበረዘው ባሕልም ይታያል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ መልኬ ያየህ በሰከላ በዓባይ መነሻ የአቡነ ዘርዓ ብሩክ ሃይማኖታዊ ክብረ ጋር ተያይዞ ለዓመታት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሲፈጸም መኖሩን አንስተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ግዮን ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ያለውን ሃብት ታሳቢ በማድረግ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በላፈ ጎብኝ እንዲስብ ተደርጎ እየተከበረ ነው ይላሉ፡፡
አካባቢው እንዲለማ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲያድግ፣ ትልቁ ሥፍራ የጎብኝዎች መዳረሻ እንዲኾን እየሠሩ መኾናቸውን ነው ያነሱት፡፡ ጎብኝዎች የዓለም ረጅሙ ወንዝ መነሻ የት ነው እያሉ እንዲመጡ? ያንም ስፍራ እንዲያደንቁ? እየተደረገ ነው ይላሉ፡፡
ክልሉ ሰላማዊ በነበረበት ወቅት በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች በስፋት ይመጡበት ነበር ነው የሚሉት፡፡ በክልሉ የተፈጠረው ወቅታዊ ችግር ግን የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ቀንሶታል ነው ያሉት፡፡ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በሀገር አሳሾች የተፈለገው የግዮን መነሻ የብዙዎችን ቀልብ ይስባል፡፡ ይመጡበት ዘንድም ይጓጉለታል፡፡
ዛሬም በርካታ እንግዶች፣ በተለይም በአቡነ ዘርዓብሩክ ጸበል ለመጸበል የሚሹ የሃይማኖቱ ተከታዮች በብዛት የሚጓዙበት ሥፍራ እንደኾነ ኀላፊዋ ነግረውናል፡፡ ቱሪዝሙ እንዲያድግ፣ ዜጎችም ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን በነጻነት እንዲፈጽሙ ችግሮችን በሰላም መፍታት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ታላቁ በዓል ዛሬ ነው፡፡ በዚህ በዓል ሃይማኖት ይሰበክበታል፡፡ የግዮን ምስጢር ይነገርበታል፣ የኢትዮጵያ ታላቅነት ይዘከርበታል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!