“ደረስጌ ማርያም ቴዎድሮስ የነገሠባት፣ ደጋጎች የሚኖሩባት”

0
254

ባሕር ዳር: ጥር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ስለዓለም ምህረት እና ሰላም ይለመንበታል። ዓለምን የናቁ ደግ እና ሩህሩህ አባቶች የምድሩን ሳይኾን ሰማያዊ ዋጋን አስበው በምሥጋና ሲደክሙ ያድሩበታል ደረስጌ ማርያም። ይህች ታላቅ ሥፍራ ሊቃውንቱ ከዓመት እስከ ዓመት ያመሰግኑባታል። ልብን በሚመስጥ ዜማ ስብሐተ እግዚአብሔር ያቀርቡባታል። በአስተርዮ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ደግሞ በብዙ ሕዝብ ትከበባለች። በሊቃውንቱ ትታጀባለች።

ደረስጌ ማርያም በአስተርዮ ማርያም ክብረ በዓል ከአራቱም አቅጣጫ በሚሠባሠቡ አማኞች ትደምቃለች። ይህ ቀን ለደረስጌ ማርያም ልዩ ነው። የጃናሞራ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቄስ መሳፍንት አማረ እንደነገሩን ደረስጌ ማርያም በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ ከመካነ ብርሃን ከተማ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

ደረስጌ ማርያም በጎንደር ዘመን በአድያም ሰገድ ኢያሱ እንደተመሠረተችም ነግረውናል። በ1818 ዓ.ም ደግሞ የስሜኑ ገዥ ራሥ ውቤ ኃይለማርያም እንደገና አንጸዋታል ይላሉ። አሁን ያለው ኪነ ሕንፃ እና ቅርስ በራስ ውቤ አማካኝነት የተገነባ ነው። ደረስጌ ማርያም ዘመነ መሳፍንትን የቋጩት፣ ለአንዲት ኢትዮጵያ አንድነት የታተሩት፣ አጼ ቴዎድሮስ በከፍታ ላይ ቆመው የተቀቡባት ታሪካዊት ሥፋራ ናት። እርሳቸው የተቀቡበት ሰገነትም በቅጥር ግቢው ውስጥ በክብር ቆሞ እንደሚገኝ ነግረውናል።

ደረስጌ ማርያም የአጼ ቴዎድሮስ ባለቤት እና የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ እናት የእቴጌ ጥሩወርቅ የትውልድ ቦታም ናት ይላሉ። ይህች ሥፋራ የዘመነ መሳፍንት ፍጻሜ የተበሰረባት ናትና በልዩ ሁኔታ ትታያለች። በዚህም ደረስጌ ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መነሻ፣ አጼ ቴዎድሮስ መናገሻ ናትና በታሪክ ስትታወስ ትኖራለች ነው የሚሉት። በወርቅ ቅብ ጉልላት አጊጣ የተሠራችው ደረስጌ ማርያም ከደጃች ውቤ እና ከዳግማዊ ቴዎድሮስ ጋር የሚገናኙ በርካታ ቅርሶችን የያዘች ቤተ ክርስቲያንም ናት፡፡

ደረስጌ ማርያም በወርቅ እና በብር የተንቆጠቆጡ ከበሮዎች፣ ከጎሽ ቀንድ የተሠሩ ዋንጫዎች፣ የነገሥታት ዘውዶች፣ የንግሥና አክሊሎች እና ሌሎችም ቅርሶች በውስጧ አቅፋ ይዛለች። የተለያዩ የወርቅ እና ብር መስቀሎች፣ የብራና መጻሕፍት እና ሌሎችም ቅርሶች በቤተ ክርስቲያኗ ይገኛሉ፡፡

ደረስጌ ጽርሐ ጽዮን ማርያም አሰገምጋሚ ድምጽ ያለው የደወል ቅርስም ባለቤት ናት። ደወሉ ያለ ቁርጥ ነገር አይደወልም ይባላል። ይህ ደወል የሚደወለው አንድም በአካባቢው ላይ አስጊ ነገር በተከሰተ ጊዜ ተጠራርቶ ለመከላከል፣ ሁለትም ፍጹም የኾነ ደስታን የያዘ ክብረ በዓል የደረሰ ዕለት ነው ይህ ደወል የሚደወለው።

ይህ አስገምጋሚ ድምጽ ያለው ደወል በዓመት ውስጥ ሁለቴ በሚከበሩ የደረስጌ ጽርሐ ጽዮን ማርያም የደስታ ቀናት ይደወላል። በሕኅር 21 እና በጥር 21 ቀናት። በደረስጌ ጽርሐ ጽዮን ማርያም ዓመታዊ የንግሥ በዓል ላይ የሀገሬው ሰው በአስገምጋሚው ደወል ድምፅ ተጠራርቶ በእልልታ እና በሆታ ይጓዛል። የንግሥናም የቅድስናም ቦታ በኾነችው ድንቋ ደረስጌ ማርያም ላይ ዕድል ቀንቶት የተገኘ ሁሉ የሚያስደንቀውን ሥርዓት ይመለከታሉ።

ቅርሶቿን ለጎብኝዎች ምቹ እንዲኾኑ ሙዚየም ተገንብቶ መጠናቀቁንም ነግረውናል። አሁን ላይ የቅርስ ማስቀመጫው እየተሠራ ነው ብለውናል። ዛሬ ደረስጌ ከሁሉ በላይ አምራ እና ተውባ በአማኞቿ አጊጣ እየከበረችም ነው። የቻሉት በአጸዷ ሥር ተገኝተው ምስጋና እያቀቡባት ነው። ያልቻሉት ደግሞ በዓይነ ህሊናቸው ያስቧታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here