“ሰማይን የመሰለች ምድር፤ ያልተፈታች ምስጢር”

0
240

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እልፍ አዕላፍ ጠቢባን በምድሯ ተነስተዋል፤ በጥበባቸውም የጥበብን ነገር አድርገዋል፤ በተሰጣቸው ጥበብ ሁሉ አሻራቸውን አሳርፈው አልፈዋል፤ ስማቸው የሚጠራበትን፣ ክብራቸው የሚነገርበትን፣ ታሪካቸው የሚዘከርበትን ጥበብም አኑረዋል፡፡ ይህች ጥበብ ግን ከተሠሩት ጥበባት ሁሉ ትበልጣለች ይላሉ አበው፡፡

አያሌ ነገሥታት አሸከሮቻቸው ይታዘዙላቸዋል፤ ለእግራቸው ውኃ እያቀረቡ ያጥቧቸዋል፤ እንቅልፍ በዓይናቸው ሳትዞር በቤተ መንግሥት ዙሪያ ቆመው ይጠብቋቸዋል፤ የሞት ፍላጻ በመጣ ጊዜም ከእነርሱ ቀድመው ይሞቱላቸዋል፤ የመከራቸውን ጽዋ ይጎነጩላቸዋል፤ በደምና በአጥንታቸው ሀገር ያሰፉላቸዋል፤ ዙፋን ያስከብሩላቸዋል፡፡

እርሳቸው ግን እንደሌሎቹ ነገሥታት አሸከሮቻቸው ብቻ አይታዘዙላቸውም፤ አሽከሮቻቸው ብቻ አይፋጠኑላቸዋውም፤ እሳቸው ዓለት ይታዘዝላቸዋል፤ እንደ አደረጉት ይሆንላቸዋል፤ እንደ ሃሳባቸው ይፈጸምላቸዋል፡፡ እንዳሉትም ያገለግላቸዋል፤ ቤተ መቅደስም አሰቡና ጠረቡት ያመረ ቤተ መቅደስ ኾነላቸው ይህም ጥበባቸው ከጠቢባን ሁሉ ያልቃቸዋል፤ ይህም ንግሥናቸው ከነገሥታት አስበልጦ ያስወድሳቸዋል፤ ይህም ክብራቸው ከተከበሩት ሁሉ ከፍ እያደረገ ያስጠራቸዋል፤ ዓለት የታዘዛለቸው፣ ድንጋይ የለዘበላቸው እየተባሉ ይጠራሉና ንጉሥ ወ ቅዱስ ላሊበላ፡፡

በዙፋን ላይ ተቀምጠው የሚፈርዱበት፣ ያማረውን ዘውድ ደፍተው የሚታዩበት፣ የተዋበችውን በትረ መንግሥት ጨብጠው የሚከበሩበት፣ በመኳንንቶቻቸው እና በመሳፍንቶቻቸው በግራና በቀኝ ታጅበው የንግሥና ዘመናቸውን የሚያጣጥሙበት ያማረ ቤተ መንግሥት መገንባት አላማራቸውም፤ ምድራዊ ደስታና ተድላ የሰማዩን ዓለም አላስረሳቸውም፡፡

አበው ቅዱስ ወ ንጉሥ ላሊበላ የጥበብ ሥራዎች ያረፉባትን ቅድስት ምድር ደብረ ሮሐን እያዩ ድንጋይ ሰው የኾነባት ምድር ይሏታል፡፡ እንደምን ኾኖ ቢሉ በዚያች ምድር ያለው ድንጋይ አንደበት እንዳለው ሁሉ ጥበብ ይናገራል፣ ታሪክ ይገልጣል፣ ሃይማኖት ያስተምራልና ይላሉ፡፡ እኒያ አብያተ ክርስቲያናት የታነጹበት ዓለት ከሰው በልጦ ይናገራል፤ ይመሰክራል፤ ታሪክ ይዘክራል፤ ክብርን ይገልጣልና፡፡

ቅዱስ ወ ንጉሥ ላሊበላ ድንጋዩን አዘዙት፣ አዝዘውም ቤተ መቅደስ አደረጉት፣ ለዘለዓለም እየመሰከረ ይኖር ዘንድ ጥበባቸውን አስቀመጡበት፡፡

ድንጋይም ሰማይ ኾነ ይላሉ አበው ስለ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሲናገሩ።

በአንድ ቋጥኝ ላይ የበዙ አብያተ ክርስቲያናትን መቅረጽ እንደምን ይቻላል? ከአንድ ቋጥኝ ሰማይን መቅረጽስ እንደምን ይኾናል? እሳቸው ግን ሁሉን አደረጉት፣ ምድርንም ሰማይ አደረጓት፡፡ ሰማይን በምድር አምጥተው ለሕዝብ ሁሉ አሳዩት፡፡

አበው ሲናገሩ ኢትዮጵያም የረቀቀው ሁሉ ተሰጣት ይላሉ፡፡

ተክለጸዳቅ መኩሪያ ኑብያ አክሱም ዛጉዬ እስከ ዐፄ ይኩኖ ዓምላክ ዘመን መንግሥት በሚለው መጽሐፋቸው ኮንቲ ሮሲኒን ጠቅሰው ስለ ላሊበላ ሲጽፉ “ ዘውድ ደፍቶ የነገሠው በቅዱስ ገብርኤል እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤትክርስቲያን ነው፡፡ በመንበረ ዳዊት ተቀምጦ ለዜጎቹ ፍርድ ይሰጣል” ብለዋል፡፡

በመንበረ ዳዊት የተቀመጡት ንጉሥ ሕዝብ እና ዘመን እንዲባርኩ የተመረጡ ቅዱስ፤ ታላቅ ታሪክ ሰርተው ሀገር እንዲያጸኑ ተቀብተው የነገሡ ንጉሥ ናቸው፡፡ ተክለ ጻዲቅ “ላሊበላ በመዘኑ የጽድቅና የመንፈሣዊ ሥራ መሥራት የዘወትር ልማዱ ነበር፡፡ በደብረ ሮሃ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናቱን ከማሳራቱ በፊት የእግዚአብሔር አብን ቤተክርስቲያን በግሸን አምባ አሠርቷል” ብለው ጽፈዋል፡፡

በገድለ ቅዱስ ላሊበላ ስለ አብያተክርስቲያናቱ እንዲህ ሠፍሯል “ ወዳጆቼ ሆይ ስመ ጥሩ በኾነ በቅዱስ ላሊበላ እጅ እሊያ አብያተክርስቲያናት ከምድር ልብ ወጥተው የሚሠሩበት ጊዜ እንደደረሰ እንግራችሁ ዘንድ ስሙ፡፡ የሕንጻቸውም ሥራ እንዴት ኾኖ ያለ እንጨት፣ ያለ መዋቅር፣ ያለ ማገር ያለ ገመድ እንዴት እንደኾነ፡፡ እንደዚህ ያለ ሰምታችኋልን? ወይም በዓይናችሁ አይታችኋልን? እንደዚህ ያለ የሚደንቅ የሚያስደንቅ ተሰውሮ ኖሮ በቅዱስ ላሊበላ እጅ የተገለጠ ሕንጻ ከልብ የረቀቀ ከሕሊናም የተሠወረ እንዲህ ያለ ሰምታችኋልን? ወይም በዓይናችሁ አይታችኋል?” ይላል፡፡ ረቂቅነቱን፣ ድንቅነቱን፣ ከሕሊና የላቀ መኾኑን ሲገልጽ፡፡

ተክለጻዲቅ መኩሪያ ፍራንቼስኮ አልቫሬዝን ጠቅሰው ጽሑፍ ሲያስቀምጡ “እነዚህን የመሠሉ የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ በዓለም ይገኝ አይመስለኝም” በማለት ጽፈዋል፡፡

የመንግሥታቸው ስም ገብረ መስቀል የተሰኙት ቅዱስ ወ ንጉሥ ላሊበላ በገድላቸው እንደተጻፈው “ የእሊያን አብያተ ክርስቲያናት ሥራ በየትኛው አንደበት መናገር እንችላለን? የቅጽራቸውንም ሥራ ለመናገር አንችልም፡፡ ይህንንስ ተውትና ውስጣቸውንም ያየ አይቶ አይጠግብም ለማድነቅም ፈጽሞ አይቻልም፡፡ መደነቂያዎቹን ቆጥሮ ያውቅ ዘንድ በዚያ ዘመን ሥጋዊ ሰው የማይቻለው በቅዱስ ላሊበላ እጅ ድንቅ ሥራ ተሠርቷልና፡፡ የሰማይ ከዋከብትን የሚቆጥር ካለ በቅዱስ ላሊበላ እጅ የተሠሩትንም ይቆጥራቸዋል” ተብሏል፡፡ እጅግ የረቀቁ እና በምስጢር የተመሉት አብያተ ክርስቲያናቱን ጨርሶ የሚያውቃቸው፣ አውቆም የሚያደንቃቸው፣ አድንቆም የሚፈጽማቸው የለምና፡፡

እነኾ ይህ የረቀቀ የጥበብ አሻራ የሚታይበት፤ የላሊበላ አምላክ እና የላሊበላ ልደት የሚከበርበት፣ ሕዝብ ሁሉ ከአራቱም ንፍቅ የሚሰባሰብበት፣ ምሥጋና እና ውዳሴ የሚበዛበት፣ እልልታው እና ዝማሬው የሚያይልበት፣ ክርስቲያኖች ሁሉ ተዝቆ የማያልቀውን በረከት ይቀበሉ ዘንድ በአጸዱ ሥር የሚሰባሰቡበት፣ የመላእክት እና የሰባ ሰገል ምሳሌ የኾነው ዝማሬ የሚዘመርበት፣ ቤዛ ኩሉ እየተባለ ውዳሴ የሚቀርብበት ቀን ቀርቧል፡፡

ልደት በደረሰ ጊዜ ክርስቲያኖች ሁሉ ቢችሉ ጌታ ወደ ተወለደባት ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ ቤተልሔም፣ ባይቻላቸው ወደ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ወደ ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ያቀናሉ፡፡ በዚያም ተሰባስበው በረከት ይቀበላሉ፤ ታሪክ እና ሃይማኖት ይማራሉ፡፡ ፍቅርና ሰላምን ያጸናሉ፡፡ አንድነትን ያነግሣሉ፡፡

በቅዱስ ላሊበላ እጅ የተሠራውን የአብያተ ክርስቲያናት ሕንጻ ሥራ ያይ ዘንድ የሚወድ ሰው ቢኖር ይምጣና በዓይኖቹ ይይ፡፡ የረቀቁትን የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ለማየት የሚወድ ሁሉ ዓይኖቹን ሁሉ ወደዚያው ያዙራቸው፣ ጀሮዎቹንም ወደ ዚያው ያዘንብላቸው፣ እግሮቹንም ወደ ላሊበላ ይምራቸው፤ በዚያች ምድር የረቀቀች ነገር አለችና አይተው ይደሰቱባታል፤ ሀሴትም ያደርጉባታል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here