ግሸን ደብረ ከርቤ

0
244

ባሕር ዳር: ጥር 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ የምትገኘው እና ዳግማዊት ኢየሩሳሌም በመባል የምትታወቀው ግሸን ደብረ ከርቤ በእምነት እና አሥተዳደር ቁርኝት የፈጠሩባት ድንቅ ምድር ናት፡፡ ሰማይ እና ምድርን የፈጠረ አምላክ የሰውን ልጅ ከባርነት ቀንበር ያድን ዘንድ በራሱ ፈቃድ ሕይወቱን የገበረበት ግማደ መስቀል መገኛ የኾነች እና የተቀደሰች ቦታ ናት።

ግሸን ደብረ ከርቤ ከሀገረ ናዝራን ወይም የመን ተነስተው እንደመጡ በሚነገርላቸው ፈቃደ ክርስቶስ በሚባሉ መነኩሴ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተመሠረተች ይነገራል። ፈቃደ ክርስቶስ ከስምንት መነኮሳት ጋር እንደመጡም ታሪክ ያስረዳል ያሉት አባ ብስራተ ገብርኤል ክፍለ ማርያም የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዋና አሥተዳዳሪ ናቸው።

እንደ አባ ብስራተ ገብርኤል ገለጻ መነኮሳቱ ከየመን ሲመጡ የእመቤታችን እና የእግዚኣብሔር አብ ታቦታትን ይዘው እንደመጡም አብራርተዋል። የእግዚአብሔር አብ ታቦት ያለበትን ቦታ የወንዶች ገዳም ሲያደርጉት የእመቤታችን ታቦት ያለችበትን ደግሞ የሴቶች ገዳም አድርገው ሲያገለግሉበት እንደነበርም በታሪኩ ተቀምጧል ነው ያሉት።

አሁን ግሸን ደብረ ከርቤ እየተባለች የምትጠራው የበረከት ቦታ መሥራቿ ፈቃደ ክርስቶስ በነበሩ ጊዜ ደብረ ነጎድጓድ ስትባል ቆይታ በኋላ ደብረ ነገሥት እየተባለች ትጠራ እንደነበር አባ ብስራተ ገብርኤል ታሪኳን አጣቅሰው ተናግረዋል። ቆይቶ በ14ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ አማካኝነት የስም ለውጥ ተደርጎ ግሸን ደብረ ከርቤ ተብላለች ነው ያሉት።

ደብረ ከርቤ ማለትም መስቀሌን በመስቀል ተራራ ላይ አስቀምጥ ከሚለው የፈጣሪ ትዕዛዝ የመጣ ሲኾን የመስቀል ተራራ ማለት እንደኾነ ነግረውናል። ግሸን ደብረ ከርቤ ስትነሳ ከሰማይ ዝቅ ከመሬት ከፍ ካለ ቦታ ላይ የመስቀሉ ዙፋን የተቀመጠበት መኾኑ ይወሳል ነው ያሉት። ዓለም የዳነበት፤ የክርስቶስ ቅዱስ ስጋው የተቆረሰበት፣ ክቡር ደሙ የፈሰሰበት ያ ታሪካዊ የሰው ልጆች የድኅነት ምክንያት ያለው ግሸን ላይ ነው ይላሉ አሥተዳዳሪው።

ታሪኩ እንሚያትተው የኢየሱስ ክርስቶስን ግማደ መስቀል አጼ ዳዊት ከሀገረ ግብጽ በእጅ መንሻ አማካኝነት ወደ ቅድስቷ ሀገር ኢትዮጵያ እንዳመጡት ይነገራል ብለዋል አባ ብስራተ ገብርኤል። ልጃቸው ዘርዓ ያዕቆብም ከእሳቸው ተቀብሎ ፈጣሪ በፈቀደለት እና ባዘዘው ቦታ ላይ እንዳስቀመጠውም ታሪኩ ያስረዳል ነው ያሉት። መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ የሚለው ትዕዛዝም ያኔ ተፈጸመ ነው ያሉት።

የግሸን ደብረ ከርቤ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ልዩ ትርጉም የሚሰጠው እና በድምቀት የሚከበርበት ታሪካዊ ቦታ ነው። ከእነዚያ ደማቅ የክብረ በዓል ቀናቶች ውስጥ ደግሞ የማሪያምን ዕረፍት የሚታሰብበት ጥር 21 ወይም አስተርዕዮ ማሪያም አንዱ ነው ብለዋል አባ ብስራተ ገብርኤል። የዚህ ዓመት የአስተርዕዮ ማሪያም ክብረ በዓል በሞቀ መንገድ ከዋዜማ ጀምሮ እየተከበረ መኾኑንም ለአሚኮ ተናግረዋል።

ገና፣ ጥምቀት እና ሌሎች ያሳለፍናቸው ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት በግሸን ደብረ ከርቤ ያማሩ እና የደመቁ ኾነው አልፈዋል ያሉት አሥተዳዳሪው ለዚህ ድምቀት ያበቃን ደግሞ በአካባቢው ሰላም መኖሩ ነው ብለዋል። ባሳለፍናቸው በዓላትም የሰላም ወዳዱ ሕዝብ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል። ወደ ግሸን የመጣው ሁሉ በሰላም ተባርኮ፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን አክብሮ የተመለሰበት እንደነበርም አስታውሰዋል።

እንግዳ ተቀባዩ የአካባቢው ማኅበረሰብም አብልቶ እና አጠጥቶ ሲሸኝ እንደነበር ጠቁመዋል። ለዚህ ሁሉ ታድያ በአካባቢያችን ሰላም መኖሩ በዓሉ የበለጠ እንዲደምቅ አድርጎት ነበርም ነው ያሉት። ዛሬ ላይ የሚከበረው የእመቤታችን የእረፍት መታሰቢያ ክብረ በዓልም የግሸን ታሪኳን እያነሳን፣ የፈጣሪን ቸርነት እያወደስን፣ አምረን እና ደምቀን የምንውልበት ነው ብለውናል።

አባ ብስራተ ገብርኤል እግዚአብሔር አምላክ ሰላምን ፈልጓት ብሏልና ሙሉ የኾነ ሰላምን በሁሉም አካባቢ ማምጣት የምንችለው እኔ እና ሁሉም ሰው ነን ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል። ሰላም ሲኖር ሀገር ትኖራለች፣ ሀገር ስትኖር ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ትኖራለች ነው ያሉት። ቤተ ክርስቲያን ሀገር ናት፤ ሀገርም ቤተ ክርስቲያን ናትና ማንኛውም ሰው የኾነ ሁሉ በየሃይማኖቱ እና በየ ዕምነቱ መጸለይ፣ ፈጣሪን መጠየቅ ያስፈልጋል እንጅ አንዱ የአንዱ ደጋፊ ለሌላው ደግሞ ገፊ መኾን ፈጽሞ የለበትም ብለዋል።

በዚህ ዘመን የምንመለከተው እና የምንሰማው ሁሉ ከፈጣሪ ሥራ ያፈነገጠ እየኾነ መጥቷልና እኛ ሰዎች ቆም ብለን እናስብ በማለት አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here