ባሕር ዳር: ጥር 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 85ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል “አርበኝነታችን ለአኹናዊ ሰላማችን”በሚል መሪ መልዕክት በደመቀ ኹኔታ በእንጅባራ ከተማ እየተከበረ ይገኛል። በዓሉ ፈረሶች እና ፈረሰኞች ለሀገር ነጻነት ሲሉ የከፈሉትን መስዋዕትነት እና የከፈሉትን ዋጋ በማሰብ የሚከበር በዓል ነው።
በዓሉ ሲከበርም አባት አርበኞች የጣሊያን ወረራን በፈረሶቻቸው ታግዘው የቀለበሱበት፣ ያመጡት ድል እና ነጻነት ይወሳበታል።
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር አለቃ ጥላየ አየነው 85ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበርን በየዓመቱ ስናከብር ነጻነታችን ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት የመጣ መኾኑን እያሰብን ነው ብለዋል።
ከሁሉም በላይ ግን ፈረስ ለአገው ሕዝብ ሁለ ነገሩ እንደኾነ ገልጸዋል። ፈረስ ለአገው ሕዝብ የልማት ማሳለጫ ሀብቱ፣ በደስታ ጊዜ መድመቂያው፣ በሀዘን ጊዜ ደግሞ ማልቀሻው እንደኾነ ተናግረዋል።
ፈረስ ለአገው ሕዝብ ትልቅ ባለውለታው እንደኾነ አስገንዝበዋል። ለፈረሶች ክብር እንደሚገባቸውም አብራርተዋል።
የአገው የፈረሰኞች ማኅበሩ በየዓመቱ እየደመቀ እና እየጎለበተ መምጣቱንም አቶ ጥላየ አየነው ተናግረዋል።
ማኅበሩ በከተማም ኾነ በገጠር በርካታ አባላትን እያበዛ ነውም ብለዋል።
በአጠቃላይ ማኅበሩ ከ6400 በላይ ኮሚቴዎች እንዳሉትም አቶ ጥላየ አየነው ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን