በባሕር ላይ የታነጸው አሰደናቂው ይምርሃነ ክርስቶስ!

0
181

ባሕር ዳር: የካቲት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አቅጣጫችንን ወደ ሰሜን ወሎ አድርገን ወደ ቡግና ወረዳ በምናብ ተጉዘናል። መዳረሻችን ደግሞ ይምርሃነ ክርስቶስ ነው። ይምርሃነ ክርስቶስን ለማግኘት ከላሊበላ ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ 42 ኪሎ ሜትር መጓዝን የሚጠይቅ ነው።

ይምርሃነ ክርስቶስ የዋሻ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ሲኾን በድንቅ ጥበብ የተሠራ ሥፍራ ነው ይላሉ በቡግና ወረዳ የባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድ መሪ ሙሉ ታደሰ፡፡ የዋሻው ወለል ስፋት 50 በ38 ሜትር ስፋት ያለው ነው የሚሉት ቡድን መሪው የዋሻው ከፍታ 7 ነጥብ 7 ሜትር የሚረዝም ሲኾን ከ996 እስከ 1036 ዓ.ም እንደታነፀ ይነገራል፡፡

የዋሻ ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራው እብነበረድን ጨምሮ ከተለያዩ ማዕድናት እንደኾነ የተናገሩት የቡድ መሪው 26 መስኮቶች እንዳሉት እና 22 መስኮቶች በውስጥ የሚከፈቱ ስለመኾናቸው አስረድተዋል፡፡ አራቱ መስኮቶች ደግሞ የማይከፈቱ ተደርገው የተሠሩ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡ ይምርሃነ ክርስቶስ አራት ፎቅ ያለው ሲኾን ውኃ ላይ የቆመ መኾኑ ልዩ እንደሚያደርገው ነው ያብራሩት፡፡

ይህን ድንቅ ቦታ ላሊበላን የጎበኘ ሳይጎበኘው እንደማይመለስም ተናግረዋል፡፡ ቅርሱ የዓለም ቅርስ መስፈርቶችን አብዛኛውን እንደሚያሟላ የተናገሩት አስተባበሪው ብዙ ጊዜ ጥናት ሲያደርጉበት መቆየታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ ይምርሃነ ክርስቶስ የቡግና ወረዳ ልዩ መገለጫ ነው። ይህንን ድንቅ ሥፍራ የሠራው ከላስታ ነገሥታት አንዱ የኾነው ይምርሃነ ክርስቶስ የተባለ ንጉሥ ነው፡፡

ይምርሃነ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለ40 ዓመታት ካሥተዳደሩ ንጉሶች ውስጥ አንዱ እንደኾነ ይነገርለታል፡፡ ይምርሃነ ክርስቶስ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት በኋላ እጅግ ውብ የኾነ የጥበብ ሥራ የታየበት የጥበበኛ እጆች ውጤትም ነው፡፡

በዙሪያው እነ ገነተ ማርያም፣ ብልባላ ጊዮርጊስ፣ ብልባላ ቂርቆስ እና መሰል ከአንድ ዓለት የተፈለፈሉ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ያሉበት ሥፍራ መኾኑ ልዩ እንደሚያደርገውም አስረድተዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here