የሀርቡ ፍል ውኃ እና የቱሪዝም ጸጋው።

0
127

ባሕር ዳር: የካቲት 10/2017 ዓ.ም(አሚኮ) ሀርቡ ፍል ውኃ በደቡብ ወሎ ዞን በሀርቡ ከተማ አሥተዳደር በ03 ቀበሌ የሚገኝ የተፈጥሮ ሃብት ነው፡፡ ከሀርቡ ከተማ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ሦስት ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ እንደተጓዙ ይገኛል፡፡

ቦታው በእስልምና ሃይማኖት እና ትውፊት መሠረት ከ700 ዓመታት በፊት ሀጂ ማሕሙድ በተባሉ የሃይማኖት አባት ለበሽታዎች ፈውስ ይኾን ዘንድ በዱዓ እንዳፈለቁት ይነገራል፡፡ ሸህ መሐመድ ሚስባህ በሃይማኖታዊ የዘር ሀረግ እንደሚተዳደር እና እርሳቸውም የ11ኛው ትውልድ መኾናቸውን ይናገራሉ፡፡

ፍል ውኃው ለተለያዩ በሽታዎች የፈውስ አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ሰዎች እምነት ሳይለዩ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየሄዱም እንደሚፈወሱበት ገልጸዋል፡፡ ለሴቶች እና ለወንዶች ለየብቻ ሆኖ የተዘጋጀ ባሕር አለው፡፡ ጽዳት፣ ሕግ እና ሥርዓት እንዲኖረው ለማድረግም ወጣቶች እየሠሩ ነው ብለውናል፡፡

መብራት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉለትም ለከተማ አሥተዳደሩ እየጠየቅን ነው ብለዋል ሸህ መሐመድ፡፡በፍል ውኃው በጥበቃ ሥራ የተሠማሩት ጀማል አወል ከጥቅምት እስከ ሰኔ ድረስ የጥበቃ፣ የጽዳት እና ተጠቃሚውን የማሥተባበር ሥራ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡ የተጠናከረ ባይሆንም በምግብ፣ በማረፊያ፣ በሱቅ፣ እና በሌሎች አገልግቶችም የተሠማሩ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ፍል ውኃው አካባቢ ንጽሕና እንደሚጎድለው ገልጸዋል። ንጽሕና በሚያጓድሉ ተጠቃሚዎች ላይ ቅጣት ለማሳረፍ ተሞክሮ እንደነበር አሰታውሰዋል። ነገር ግን ማስተማር እንጂ ቅጣት አስተማሪ አይደለም በሚል መቅረቱን ተናግረዋል፡፡ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲያበጅለትም ጠይቀዋል።

ከአንድ ተጠቃሚ እስከ 30 ብር በሚከፈል ገቢ ማሥተዳደር አስቸጋሪ መኾኑን ነው የገለጹት። ገቢ ከሌለው ደግሞ ጥበቃ እና አሥተባባሪዎች በመሰላቸት ከማገልገል ይርቃሉ ነው ያሉት፡፡ ፍል ውኃው አገልግሎቱ የበለጠ እንዲቀጥል በአደረጃጀት እና በአገልግሎት ማደግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን የቃሉ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ አወል መሐመድ 40 የሚኾኑ ወጣቶች ተደራጅተው የንጽሕና እና የጥበቃ አገልግሎት እየሰጡ መኾናቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን ንጽሕናውን እና ወሰኑን በማስከበር በኩል ውስንነት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ከሥራና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ጋር በመነጋገር ወጣቶቹ ሠልጥነው ሁለገብ አገልግት እንዲሰጡ ለማድረግ መታሰቡንም አንስተዋል፡፡ ከጥቅምት እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ሰዎች ለመፈወስ ይመጣሉ፤ ጸጋውንም ይጎበኛሉ ያሉት ባለሙያው መሠረተ ልማት ቢሟሉለት የበለጠ ይጠናከራል ብለዋል፡፡ ፍልውሃውን ለማስተዋወቅም የተለያዩ አማራጮች እየተተገበሩ መኾኑን አንስተዋል፡፡

የሀርቡ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሕመድ አደም ከተማ አሥተዳደሩ በቅርብ ጊዜ በመቋቋሙ እና ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ስለሌለው ፍል ውኃው በቂ እንክብካቤ እንዳልተደረገለት ነው የገለጹት፡፡

በቦታው መሠረተ ልማት ባለመኖሩም ተገልጋዮች የሚያርፉት ርቀው ሄደው እንደኾነም ነግረውናል፡፡ ከዞን እና ከክልልም የሥራ ኀላፊዎች እየመጡ ቢያዩትም በጸጋው ልክ ወደ ሥራ እንዲገባ አልተደረገም ነው ያሉት፡፡ ከተማ አሥተዳደሩ የበኩሉን መፍትሔ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ይድነቃቸው ጌታነህ በዞኑ ዘጠኝ የከተማ አሥተዳደሮች የቱሪስት መስህብ ሃብት እንዳላቸው አንስተዋል። ነገር ግን የባሕል እና ቱሪዝም ተቋም ስለሌላቸው ሃብቱን አልምቶ ለመጠቀም ውስንነት መኖሩን ገልጸዋል፡፡

የገጠር ወረዳ እና የዞን ባለሙያዎችን ማሠራት በጊዜያዊ መፍትሔነት እንደተጠቀሙም አንስተዋል፡፡ ለዘላቂ የዘርፉ ልማት ግን ከተማ አሥተዳደሮቹ መዋቅር እንዲፈቀድላቸው ለክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ የተዋቀሩ የገጠር እና ከተማ አሥተዳደሮች ያላቸውን የቱሪስት መስህብ ሃብት በማጥናት ባለሙያ እንዲፈቀድ ለክልሉ መንግሥት እና ለሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ጥያቄው መቅረቡን ከአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here