ደጀን ከተማ

0
297

ባሕር ዳር: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልላችን መውጫ እና መግቢያ በር ያላት የባለብዙ እምቅ ሀብት ባለቤት ደጀን ከተማ በምስራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኙ 17 ወረዳዎች እና 9 የከተማ አሥተዳደሮች መካከል አንዷ ናት፡፡

👉 ከአዲስ አበባ 229 ኪሎ ሜትር
👉 ከባሕር ዳር 335 ኪሎ ሜትር
👉 ከደብረ ማርቆስ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች ደጀን ከተማ፡፡

ደጀን ከተማ አማካይ የዝናብ መጠኗ ከ800 እስከ 1200 ሚሊ ሜትር ይደርሳል። የሙቀት መጠኗ 23 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የኾነ ለሰው ልጅ ኑሮ በጣም ተስማሚ እና ምቹ የአየር ንብረት ያላት ከተማ ናት፡፡ የደጀን ከተማ የመሬት አቀማመጥ በአብዛኛው ሜዳማ ሲኾን ከባሕር ጠለል በላይ ከ1002 እስከ 2586 ሜትር ከፍታ ተቀምጣለች። የከተማዋ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ በዓባይ ሸለቆ የተከበበ ነው፡፡

ደጀን ከተማ የሰሜኑ ክፍለ ሀገር መግቢያ በር እና ደረቅ ወደብ ስለኾነች የብዙ ተሸከርካሪዎች እና ጎብኝዎች ማረፊያ፣ መተላለፊያ እና ማደሪያም በመኾኗ ለከተማዋ ነዋሪዎች ዋና የገቢ ምንጭ ናት፡፡ በ1929 ዓ.ም የተመሠረተችው ደጀን ስያሜዋ “ውሻ ጥርስ” ይባል እንደነበር እና ይህን ስያሜ ያገኘችው የጥንታዊ የቤት አሠራር ቅርፅ የውሻ ጥርስ መሰል ስለነበር እንደኾነ አፈ ታሪክ ያስረዳል፡፡

በ1930ዎቹ ጣሊያን ሀገሪቱን በወረረችበት ወቅት ከአዲስ አበባ ደብረ ማርቆስ ይጓዙ በነበሩ ነጋዴዎች የአሁኑን ደጀን የሚለው ስያሜ እንደሰጧትም ይነገራል፡፡ ደጀን ከተማ እንደ ከተማ እውቅና አግኝታ በ1936 ዓ.ም ማዘጋጃ ቤት ተቋቋመላት፡፡ በ1939 ዓ.ም የቤተ ክህነት ትምህርት እውቅና በነበራቸው መሪጌታዎች በዘመናዊ መልክ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት በሳር ቤት ተጀመረ፡፡

በዓመቱም በ1940 ዓ.ም ከተማዋ የስልክ (የሬድዮ ስልክ) ተጠቃሚ ኾነች፡፡ መኖሪያቤቶች፣ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች እና ተቋማት ሥርዓት ይዘው የራሳቸው ሕጋዊ እና በቂ ቦታ ይኖራቸው ዘንድ በ1941 ዓ.ም ከተማዋ የሽንሸና ፕላን ተጠቃሚ እንድትኾን ተደርጓል፡፡

በ1970 ዓ.ም የከተማዋ ሕጋዊ የከተማ ፕላን ተሠራ፡፡ በዚሁ ዓመት ቀደም ሲል የቤተክህነት እውቀት በነበራቸው መሪጌታዎች የተጀመረው የ1ኛ የመጀመሪያ ደረጃ ዘመናዊ ትምህርት አድጎ እና ጎልብቶ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተቋቋመ፡፡

የደጀን ከተማ አሥተዳደር ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ራሷን ማሥተዳደር ጀምራለች፡፡ ደጀን ከተማ በተፈጥሮ አቀማመጧ የታደለች ስትኾን ምንም እንኳ ዋና የገቢ ምንጯ ንግድ ቢኾንም የብዙ ሰዎች እና ተሸከርካሪዎች መተላለፊያ፣ ማደሪያ እና ማረፊያ ስለሆነች ከቱሪዝም ልማት የሚገኝ ገቢዋም ከፍተኛ ነው፡፡
በከተማዋ የተጠና ማዕድን ሃብት ባይኖርም በዙሪያዋ በሚገኙ ቀበሌዎች ላይምስቶን ፣ሳንድስቶን (አሽዋማ) ሲሊካሳንድ ፣ ካልሳይት፣ ኖራ ድንጋይ፣ እብነበረድ፣ ሸክላ አፈር እና ጥቁር ድንጋይ ይገኛል፡፡ የከተማዋ አብዛኛው ነዋሪ በንግድ የተሰማራ ነው።

ከተማዋ በዙሪያዋ በሚገኙ አካባቢዎች የተለያዩ ማዕድናት በመኖራቸው እና የደረቅ ወደብ ከተማ በመኾኗ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ያደርጋታል፡፡ ይህን በመጠቀም በአሁኑ ሰዓት ባለሃብቶች እና በአክሲዮን የተደራጁ ግዙፍ ተቋማት ፋብሪካዎችን፣ ሆቴሎችን፣ የገበያ ማዕከላትን እና ማደያዎችን ቦታ ተረክበው ግንባታቸውን በመገንባት ላይ ናቸው። አጠናቅቀው ወደ ሥራ የገቡት ፋብሪካዎች ደግሞ ለዜጎች የሥራ እድል ፈጥረው ይገኛሉ፡፡

ምንጭ፡- የደጀን ከተማ ፕላን ኮሚሽን
እና
የደጀን ከተማ የአቅም ግንባታ ሕዝብ እና ሚዲያ ግንኙነት ቡድን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here