ባሕር ዳር: የካቲት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በርካታ ሀገረኛ ቁሶች በሀገር በቀል ዕውቀት እና መሳሪያ ይሠራሉ። ሀገር በቀል በኾነው ወስፌ ግራምጣን ወይም አክርማን በማዋደድ አገልግል ይሰፋል። አገልግል የባሕር ዳር መታዎቂያ መኾኑን ልብ ይሏል። በባሕር ዳር ከተማ የሚሰፋው መሶብም የባሕር ዳር መለያ ኾኗል።
ግራምጣው ወይም አክርማ በቀለም ይነከርና ኀብር እንዲኾን ይደረጋል። በኀብር የሚሰፋው መሶብ እና አገልግል ለዓይን ማራኪ ነው። መሶብ እና አገልግል ትልቅ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ኾኖ ይሰፋል። ያለ ኀብር ( አለላ ) የሚሰፋውን አገልግል የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች የተለያዬ ቀለም ባለው የቆዳ ውጤት ያስውቡታል።
‘መለጎም’ ይባላል። የተለጎመ መሶብ እና አገልግል ደግሞ ዐይነ ግቡ ነው። የቱሪስቱን ትኩረትም የመሳብ አቅሙ ከፍተኛ ነው። እንደ አገልግል ኹሉ ባሕላዊ የስፌት ውጤት የኾነው ሙዳይ የባሕር ዳር መገለጫ ነው። ከግራምጣ እና ከአክርማ ተሰፍቶ ይዘጋጃል። ሙዳይ ውብ በኾነው አለላ ወይም ክር በመሰፋቱም የዓይን ማረፊያነቱ ከፍተኛ ነው። ገንዘብ እና እንደ ወርቅ ያሉ ውድ ቁሶች ይቀመጡበታል። ሙዳይ ለመያዝ ቀላል በመኾኑ በውጭ ሀገር ዜጎች ዘንድ ተመራጭ ነው።
ኩርሲ (ወንበር) ሌላው የባሕር ዳር ቀለም ነው። የጣና ሐይቅ እና የዓባይ ወንዝ በረከት የኾነው ደንገል ተሰብዞ ይዘጋጃል። የተለያዬ ቀለም ባለው የቆዳ ውጤቶችም ተዥጎርጉሮ ይለጎማል። ኩርሲን ከኢትዮጵያውያን ባለፈ የውጭ ሀገር ዜጎችም የዓይናቸው ማረፊያ እና ተመራጭ ያደርጉታል።
የባሕር ዳር ዕደ ጥበበኞች ከቆዳ ውጤቶች ቀበቶ፣ ቦርሳ፣ ጫማ ፣ ሰገባ ፣ ዝናር ፣ የሕጻናት፣ የአዋቂዎች፣ የሴት እና የወንድ በባሕላዊ መንገድ ሠርተው የሚያቀርቡት አልባሳት እና ኮፍያ ለባሕር ዳር ተጨማሪ ፈርጥ ኾኗታል። ባሕር ዳር ከተፈጥሯዊ ውበቷ ባሻገር በጥበብ ውጤቶችም የተዋበች ናት ቢባል የሚመሰክረው ያዬ ነው። “ያዬ ይመስክር” እንደተባለ ምስክሩ ባሕርዳርን ያዬ ነው።
እነዚህ በሀገር በቀል ዕውቀት የተሠሩ የባሕር ዳር መገለጫ ባሕላዊ የስጦታ ዕቃዎች የውጭ ሀገር ጉብኝዎችን አስደምመዋል። የገቢ ምንጭም ኾነዋል። አቶ ይደግ በቃሉ አገልግል በቆዳ አስውበው በመሸጥ ቤተሰብ ያሥተዳድራሉ። ዕደ ጥበበኛው በ”ጥርን በባሕርዳር” ኤግዚቢሽን የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል። ገበያችን ተነቃቅቷል ነው ያሉት።
ወይዘሮ ይመኙሻል ዋለ በበኩላቸው የሚሠሩትን የኩርሲ ወንበር እና ባሕላዊ የስጦታ ዕቃዎች ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በጅምላ በመሸጥ ጥሩ ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው በባሕር ዳር የሚሠሩት የዕደ ጥበብ ውጤቶች ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ገጽታን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ወግ እና ልማድ ለትውልድ በማሸጋገር ረገድም ሚናቸው ከፍተኛ እንደኾነ ገልጸዋል። የቱሪስት መስህብ በመኾኑም የከተማውን ኢኮኖሚ አነቃቅተዋል ነው ያሉት። ዘርፉ በትኩረት ከተሠራበት ለከተማዋ ብሎም ለክልሉ ትልቅ የገቢ ምንጭ ሊኾን እንደሚችልም ተናግረዋል። የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ነው ያሉት።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!