ባለትልቅ አሻራዋ ደብረታቦር!

0
169

ባሕር ዳር: የካቲት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪካዊቷ እና ጥንታዊቷ ደብረ ታቦር ከተማ በ1327 ዓ.ም በአጼ ሰይፈ-አርዕድ ነው የተመሰረተችው። ለበርካታ ዓመታት የማዕከላዊ መንግሥት መቀመጫ በመኾን አገልግላለች። ተስማሚ የአየር ንብረትን ከጣና እና ከጉና አዋሕዳ የምትመግብ፤ የአየር ንብረት ተስማሚነቷ እና ተፈጥሯዊ አቀማመጧ ለረጅም ዓመታት የማዕከላዊ መንግሥት መቀመጫ እንድትኾን አድርጓታል።

በዘመነ መሳፍንት ወቅት ለመሳፍንቶች ተመራጭ ከተማ እንደነበረች የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ከዘመነ መሳፍንት መክሰም በኋላም ታላቁ ንጉሥ አጼ ቴዎድሮስ ወደ ዋና ከተማነት አሳድገዋታል። ከተማዋ ንጉሡ ያላቸውን የጥበብ እና የቴክኖሎጂ ፍላጎት ያሳዩበት የመጀመሪያው የብረት ኢንዱስትሪ የተገነባበት እና የሴቫስቶፖል መድፍ የተሠራበት ጋፋት መገኛም ናት፡፡

በከተማዋ በአራቱም አቅጣጫዎች የቤተ መንግሥታት አሻራ አኹንም እንዳሉ ሲኾን የአጼ ሰርጸ-ድንግል፣ የአጼ ሱስንዮስ፣ የአጼ ቴዎድሮስ እና የአጼ ዮሐንስ ቤተ መንግሥታት ለአብነት ይጠቀሳሉ። ደብረ ታቦር ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ብጡል የተወለዱባት እና ለሀገር ቁም ነገርን የቀሰሙባት ከተማ ናት። በኢትዮጵያ ብቸኛው የተክሌ አቋቋም ዜማ ማስመስከሪያ መገኛም ናት፡፡

ከተማዋ ብዙ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ኩነቶች ያሏት እና የምታስተናግድ ናት። የሰማዕቱን ቅዱስ መርቆሬዎስ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ የቄንጠኛ ፈረሰኞች ሽምጥ ግልቢያ እና የጉግስ ጨዋታ፤ የአሸንድዬ እና የቡሔ ደብረ ታቦር በዓላት የከተማዋ መገለጫዎች ናቸው። ቱባ ባሕል፣ ብዙ ታሪክ፣ ውብ ተፈጥሮ፣ ጀግና እና ሀገር ወዳድ ሕዝብ የሚኖርባት ደብረ ታቦር ከተማ በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ወደ ሪጅኦፖሊታን ከተማነት ማደጓን ተከትሎ በሦሥት ክፍለ ከተሞች እና በአስራ ሦሥት ቀበሌዎች ተደራጅታለች።

በከተማ አሥተዳደሩ ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እየተሠሩ የሚገኙ ሲኾን በእድሜዋ እና በታሪኳ ልክ ያልለማች በመኾኗ የሚመለከታቸው የፌደራል እና የክልል አካላት በትኩረት ይዘው ሊሠሩ እንደሚገባ አሥተዳደሩ ጥሪ አቅርቧል። ከተማ አሥተዳደሩ “ለደብረ ታቦር ሰላም እና ልማት በጋራ እንሥራ!” ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

መረጃው የደብረታቦር ከተማ ኮሙኒኬሽን ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here