ባሕር ዳር፡ ታኅሳሥ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወይና ደጋ የአየር ንብረት አለው። ጥቅጥቅ ያለው ደንም ለጣራ ገዳም ተፈጥሮ ከለገሰችው በረከቶች መካከል ዋነኛ መገለጫ ነው። በውስጡ በርካታ ሀገር በቀል ዛፎችን አምቆ እና ጠብቆ የያዘ መኾኑ “የደን ባንክ” ለመኾኑ ምስክር ነው።
በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኘው ጣራ ገዳም
ከአዲስ ዘመን ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ከባሕር ዳር ወደ ጎንደር ከሚወስደው ከዋናው መንገድ በስተግራ ከሁለት እስከ ሶስት ኪሎሜትር ገባ ብሎም አስደናቂዎቹ የዋሻ እንድሪያስ እና የወይን ዋሻ ተክለሃይማኖት ገዳማት ይገኛሉ።
ከጅምሩ የተፈጥሮ ዋሻ የሆነው፤ የዋሻ እንድሪያስ ቤተክርስቲያን የክርስትና ሃይማኖት በአፄ ኢዛና ዘመነ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ እና ከመስፋፋቱ በፊት የኦሪት እምነት ይሰበክበት እንደነበር ይነገራል።
በአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ አቡነ እንድሪያስ የተባሉ መንፈሳዊ አባት ቶማስ ከተባለ እና ከሌሎች ተከታዮቻቸው ጋር ወደ ዋሻው በመምጣት ስፍራውን የክርስትና ሃይማኖት ማስተማሪያ እንዳደረጉት የአካባቢው ካህናት እና ነዋሪዎች ይገልፃሉ።
ዋሻ እንድሪያስ ውስጥ ለውስጥ ረዥም ርቀት እንዳለው ይነገራል። የውስጥ ለውስጥ መንገዱ ተክለሃይማኖት በተባሉ የሃይማኖት አባት ስም ከሚጠራው ወይን ዋሻ ጋር እንደሚያገናኝ እና ሁለቱ መንፈሳዊ አባቶች በዋሻው ውስጥ ለውስጥ እስከ ዜና ማሪያም (አዲስ ዘመን ከተማ መውጫ) ድረስ እየተጓዙ ያስቀድሱ እንደነበር ይነገራል። የሁለቱ ዋሻዎች መገናኛ አጓት ማፍሰሻ በሚል ይታወቃል።
በደን ተሸፍኖ ገደል ስር የሚገኘው የዋሻ እንድሪያስ ቤተክርስቲያን፤ አራት የሳንቃ በሮች አሉት። በሮቹም የሴት፣ የወንድ፣ የጨዋ እና የቄስ በር ተብለው ይጠራሉ። ከዋሻው መሃል ስፋት ያለው የውሃ አካል እና ከጀርባው ደግሞ የነዋየ ቅዱሳን ማስቀመጫ ልዩ ስፍራ እንዳለው የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች ያስረዳሉ።
የሌሊት ወፎች በሚበዙበት እና ብርሃን በደበዘዘበት የዋሻው ውስጣዊ ክፍል ሁለት የእንጨት ገበቴዎች፣ የድንጋይ ደወል፣ ጽላቶች እና የብራና መጻሕፍት እንዲሁም ረዥም ዓመታትን ያስቆጠሩ የሰው አፅሞች ባንድነት ተከማችተው ይገኛሉ። በዋሻው ግድግዳ ላይም የተለያዩ ምስሎች ይታያሉ።
የዋሻው ርዝመት ከ20 ኪሎ ሜትር እንደማያንስ የአካባቢው ነዋሪዎች ይገምታሉ። ይህም የዋሻ አጥኝ ምሁራንን እና የታሪክ ተመራማሪዎችን ለሰፊ ጥናት ሊጋብዝ ይችላል።
በጣራ ገዳም አካባቢ የሚገኘው ሌላው ዋሻ ደግሞ ዙሪያውን በደን እና በገደል የተከበበው ወይን ዋሻ ተክለሃይማኖት ነው። የቤተክርስቲያኑ ሥራ በአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት ተጀምሮ፤ በአፄ ሰይፈ አርዕድ (ከ1336 እስከ 1363 ዓ.ም) እንደተጠናቀቀ ይነገራል።
ጣራ ገዳም ከሃይማኖታዊ ታሪኩ በተጨማሪ የሀገር በቀል ዛፎች ባንክ ነው። ጣራ ገደም መጎብኘት ከሃይማኖታዊ ፋይዳው በተጨማሪ መንፈሳዊ እርካታን ይሰጣል። በኩር ጋዜጣ የመረጃ ምንጫችን ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!