መንቆረር – ደብረ ማርቆስ

0
413

ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከባሕር ዳር 254 ኪሎ ሜትር፣ ከአዲስ አበባ ደግሞ 304 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። በ1845 አካባቢ በደጃች ጎሹ ዘመን በገጠር መንደርነት ተጀምራ በደጃዝማች ተድላ ጓሉ ወደ ከተማነት እንዳደገች ይነገራል፤ ቀደምቷ መንቆረር፣ የአሁኗ ደብረ ማርቆስ ከተማ።

በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው የከተማዋ ስያሜ አካባቢውን በርስትነት ያሥተዳድሩ በነበሩት “ሳርን” በተባሉ ባላባት ልጆች በአንደኛው ስም “መንቆረር” እንደኾነ ይነገራል።

መንቆረር የሚለው ስያሜ ወደ ደብረ ማርቆስ የተቀየረው ደግሞ በንጉሥ ተከለ ሃይማኖት ነው። ይህም አጼ ዮሐንስ በ1873 ዓ.ም ከነበሯቸው አራት ጽላቶች የቅዱስ ሚካኤልን ለራሳቸው በማስቀረት፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ለንጉሥ ምኒልከ፣ የቅድስት ማርያምን ለአማራ ሳይንት እና የቅዱስ ማርቆስን ለንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከመስጠታቸው ጋር ይያያዛል፡፡

ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከንጉሠ ነገሥቱ የተሰጣቸውን የመልዕልተ አድባር ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን መንቆረር እንዲተከል አደረጉ። ቤተ ክርስቲያኑ “መልዕልተ አድባር ደብረ ማርቆስ” ተብሎ እንዲሰየም በመወሰን ሕዝቡ አዲሱን የከተማ ስያሜ እንዲቀበለው በአዋጅ አስነገሩ፡፡ ከአዋጁ በኋላ የከተማዋ እና አካባቢው ስያሜ ቀስ በቀስ ደብረ ማርቆስ በሚል ሥም እየተጠራ ሄደ።

ደብረ ማርቆስ ከተማ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በጥር/1872 ዓ.ም ከነገሡ በኋላ በ1874 ዓ.ም በተተከለው የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ስያሜውን አግኝቶ እስካሁን ድረስ እየተጠራ ይገኛል፡፡ ደብረ ማርቆስ በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ጎጃም፣ ዳሞት፣ አገው ምድር እና ባሕር ዳር አካባቢ ተብለው ሲጠሩ የነበሩት ግዛቶችን በአንድ እንዲጠቃለሉ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ኢህአዴግ ሥልጣን እስከ ያዘበት ዘመን ድረስ የጎጃም አሥተዳደር ዋና ከተማ በመኾን ለረጅም ዘመን አገልግላለች፡፡ አሁን ላይ ደግሞ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ኾና በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡

ከተማዋ ስያሜዋን ያገኘችበት የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን፣ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግሥት እና አደባባይን ጨምሮ በርከት ያሉ የመስህብ ሀብቶች በደብረ ማርቆስ ይገኛሉ።

በዙሪያዋ ደግሞ እንደ አባ አስራት ገዳም፣ ውርግርግ ፋፋቴ፣ የዓባይ የተፈጥሮ ፍል ውኃ፣ ብሔረ ህያዋን ቅድስት ሥላሴ አንድነት ገዳም፣ ደብረ ገነት አቦ ቤተ ክርስትያን፣ አባ ፈቂህ ያሲን ክብረ በዓል፣ የደብረ ኤሊያስ ቤተ ክርስቲያን፣ አንቀጸ ብፁዓን ቅዱስ ላሊበላ አንድነት ገዳም፣ ሙቀት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፣ እንዶዳም ኪዳነ ምህረት፣ አጋምና ጊዮርጊስ፣ የሞላሌ ዋሻ፣ የእግዜር ድልድይ እና ቀቢ ፏፏቴ የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ እና ባሕላዊ የመስህብ ቦታዎች እንደሚገኙ የአማራ ድንቅ ምድር መጽሐፍ መረጃ ያሳያል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here