ቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሔራዊ ፓርክ!

0
233

ባሕር ዳር: የካቲት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቦረና ሳይንት ወረሂመኑ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ወሎ ዞን ስድስት ወረዳዎችን ማለትም ቦረና፣ መሃል ሳይንት፣ ሳይንት፣ ለጋምቦ፣ መቅደላ እና ተንታ ወረዳዎችን ያካለለ ነው። በእነዚህ ወረዳዎች ስር የሚገኙ 34 ቀበሌዎችን የሚያካልል ድንቅ ተፈጥሯዊ ሃብትም ጭምር።

👉 ከአዲስ አበባ በደጀን ብቸና-መርጦ ለማርያም -መካነሰላም መንገድ 461 ኪሎ ሜትር፤ ከባሕር ዳር በሞጣ -መርጦ ለማሪያም – መካነ ሰላም መንገድ 298 ኪሎ ሜትር፤ እና ከደሴ- መካነ ሰላም 198 ኪሎ ሜትር ጉዞ በኋላ ከመካነ ሰላም በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

👉 ከፍታዉ ከባሕር ወለል በላይ ከ1900 እስከ 4280 ሜትር የሚኾን ሰፊ ሥርዓተ ምኅዳርን ያቀፈ የብዝኃ ሕይዎት ባለቤት ነዉ፡፡

👉 የቦረና ሳይንት ወረሂመኖ ብሄራዊ ፓርክ በምዕራብ ወሎ ቀጣና ከሚገኙት ተራሮች እና የተፈጥሮ ደኖች አካል ሲኾን መነሻዉ “ምን ይዋብ” ተብሎ ይጠራ የነበረው እና በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ (1434-1468) ጥብቅ የንጉስ ደን የነበረ፣ በ1950ዎቹ የመንግሥት ደን ይባል የነበረ በኋላም በ1980ዎቹ ዋና የመንግሥት ጥብቅ ደን ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ነው።

👉 በ2001 ዓ.ም 4575 ሄክታር መሬት በመሸፈን በቦረና፤ በሳይንት እና መሃል ሳይንት ወረዳዎች በ13 ቀበሌዎች ተካሎ በአማራ ክልል ምክር ቤት ዝክረ ሕግ 69/2000 ሕጋዊ እዉቅና አግኝቷል፡፡

👉በ2004 ዓ.ም ደግሞ እንደገና የማጥናት እና የማካለል ሥራ ተሠርቶ በአራት ወረዳዎች ማለትም በሳይንት፣ በመቅደላ፣ በተንታ እና በለጋምቦ ወረዳዎች እና 21 ቀበሌዎችን በማካለል ወደ 15ሺህ 262 ሄክታር በማስፋት እና በማሳደግ በዝክረ ሕግ 155/2009 ዳግም ሕጋዊ እውቅና እንዳገኘም ተገልጿል፡፡

👉 ፓርኩ በትልልቅ ዕድሜ ጠገብ ሀገር በቀል ዛፎች የተሸፈኑ የቡቄ፣ የግሸዋ፣ የአለባቸዉ ዋሻ፣ ቦቃ ዋሻ፣ የነጭ ሃሮ፣ የጥር ወንዝ እና ሌሎች ዳገታማ እና ገደላማ ቦታዎችን አቅፎ ይዟል።

👉አስታ፣ የሃበሻ ጽድ፣ ወይራ፣ ውልክፋ፤ ኮሶ፣ ጅብራ፣ ችብሃ፣ አምጃ እና ጓሳ በስፋት የሚገኙ የዕጽዋት አይነቶች ናቸው።

✍️በአጠቃላይ 496 የሚኾኑ የእጽዋት ዝርያዎችንም ይዟል። ከእነዚህም ውስጥ 12 ብርቅዬ እና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው።

✍️ከ23 በላይ ዝርያዎች አጥቢ የዱር እንስሳት ይገኙበታል። ጭላዳ ዝንጀሮ፣ የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ እና የምኒሊክ ድኩላ የተባሉት በፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ።

✍️ 77 የአዕዋፋት ዝርያዎችን በውስጡ የያዘ ነው። ከእነዚህም ውስጥ አራቱ ብርቅዬ መኾናቸውንም ከአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here