በሚሊዮኖች የምትጎበኘው ደብረ ምጥማቅ ጻድቃኔ ማርያም

0
214

ባሕር ዳር: የካቲት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ)

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በሞጃና ወደራ ወረዳ የምትገኘው የጻድቃኔ ማርያም መካነ ቅዱሳን ገዳም በሰላ ድንጋይ ከተማ አቅራቢያ ትገኛለች። ቦታው ከክልሉ ርእሰ ከተማ ባሕር ዳር 767 ኪሎ ሜትር፣ ከአዲስ አበባ 202 ኪሎ ሜትር እና ከዞኑ ርእሰ ከተማ ደብረ ብርሃን 72 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ይህ ቅዱስ ሥፍራ በአፄ ዘርዓያዕቆብ እንደተቆረቆረ ሊቃውንቱ ይናገራሉ ። ጽላቷ ወደቦታው ስትመጣ ንጉሠ ነገሥቱ በእልልታና በደስታ ተቀብለው በዘመኑ ለነበሩት ካህናትና ዲያቆናት አስረከቧቸው፡፡ ቀጥሎም አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ጅባት ከተባለው ከተማ ወደ እንጦጦ አምጥተው ለብዙ ጊዜ አስቀምጠዋታል፡፡ እንደገናም ከእንጦጦ አንስተው ወደ ደብረ ብርሃን አመጧት። ከዚያም አሁን ወዳለችበት አካባቢ ወደ ሰላ ድንጋይ ሞሊያ በተባለው ከፍተኛ ቦታ ለብዙ ዓመታት መቆየቷን የገዳሟ መረጃ ይጠቁማል።

ንጉሡ በአካባቢው በሚገኘው ውኃ ላይ አፈር ጨምረው በማድረቅ ቤተ ክርስቲያኑን ሠርተውታል የሚል አፈ ታሪክ እንዳለ የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ፡፡ ጽላቷን ወደቦታው ይዘው የመጡት አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የተባሉ አባቶች እስከ ዘመን ፍፃሜያቸው ሲያገለግሉ ቆይተው በዚሁ በደብረ ምጥማቅ አርፈዋል፡፡ መቃብራቸውም በዚያው ስፍራ የሚገኝ ሲኾን አንዱ የጉብኝት ቦታም ኾኖ ኾኖም ቱሪስቶችን እየሳበ ነው።

ቤተክርስቲያኗ ከታነጸች ከብዙ ዓመታት በኋላ ንጉሡ ንዋዬ ቅድሳትን እና አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያንን ንብረት በሙሉ ከጥቃት ለመከላከል በማሰብ አሁን ወዳለበት ፃድቃኔ ማርያም ዋሻ እንዳስጠለሉት የገዳሙ ታሪክ ይናገራል፡፡ ይህም ሀብቶችን በዘመኑ ከነበረው ጥቃት የተከላከለ ሲኾን ቤተክርስቲያኗ አሁን በዋሻ ውስጥ ላላት ልዩ አቀማመጥም አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ዘመን ተሻጋሪ ኾና የተገነባችው ቤተ ክርስቲያን በዕድሜ እርጅና ምክንያት ፈርሳ ስለነበር ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ አንድ ጣሊያናዊ መሐንዲስ ልከው አሁን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን መቅደስ በዘመናዊ መልክ እንዳሠሩትም ታሪኳ ይጠቁማል። ገዳሙ በጥንቱ ይዞታ ላይ ለምዕመናን ማረፊያና አዳራሽ በመሥራት በተሻለ መልክ እያማረ መጥቷል፡፡

የሞጃና ወደራ ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያመላክተው ይህ ቦታ ለወረዳው ሕዝብ ከፍተኛ የቱሪዝም ተጠቃሚነትን እያስገኘ ነው። ወደ አካባቢው ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚመጣው የጎብኝ ቁጥርም በዓመቱ ውስጥ ከ800 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችልም የወረዳው መረጃ ያመላክታል።

አካባቢው ተጨማሪ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችን ይፈልጋል። ይህ ከኾነ ቦታው ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ በተጨማሪ ለክልሉ እና ለሀገርም የሚተርፍ የቱሪዝም ጠቀሜታ ያለው ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here