ውቡ የሾንኬ መንደር

0
128

ባሕር ዳር: የካቲት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሾንኬ መንደር ከከሚሴ ከተማ በምሥራቅ አቅጣጫ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በደዋ ጨፋ ወረዳ ጅሮታ በሚባል ቀበሌ የሚገኝ ታሪካዊ መንደር ነው። ከአርጎባ ብሔረሰብ መኖሪያ ቦታዎች ውስጥ አንዱ ነው።

ይህንን ድንቅ መንደር ሼህ ፈቄ አሕመድ የተባሉ የሃይማኖት አባት እንደመሰረቱት ይነገራል፡፡ ተራራማ ቦታ ላይ በድንጋይ፣ በአፈር እና በወይራ እንጨት በተለየ መንገድ የተሠራ መንደር ነው። ውቡ መንደር ሦስት መስጅዶች እና አምስት መቶ የሚኾኑ መኖሪያ ቤቶችን ይዟል።

የአርጎባ ብሔረሰብ ታሪክ አዋቂዎች እንደሚናገሩት አርጎባዎች በአካባቢው እንደሰፈሩ አርባ ያህል መስጅዶችን ገንብተው ነበር። ይሁን እንጅ የዕድሜ ጫናን ተቋቁመው ማለፍ የቻሉት ጥቂቶች ናቸው።

በመንደሩ የሚገኙ አብዛኞቹ ቤቶች በአራት ማዕዘን ቅርጽ የተሠሩ ናቸው። ውስጣዊ ገጽታቸው ማራኪ ከመሆኑ ባሻገር ሙቀት እና ቅዝቃዜን በመመጠን ለኗሪዎች ምቾትን ያላብሳሉ። የቤቶች ጣርያ በእንጨት ርብራብ ላይ በድንጋይ እና ጭቃ ወይም አፈር በሥርዓት የተሞላ በመኾኑ ለመናፈሻነት ያገለግላል፡፡

ይሄም ጎብኝዎች ከቤቶቹ ጣሪያ በመውጣት የአካባቢውን መልከዓ ምድር ለመቃኘት አመች አድርጎታል። ሾንኬ ለረዥም ዓመታት የእስልምና ትምህርት ሲሰጥበት የቆየ አካባቢ ነው። ጁሃር ሃይደር ቤን አልይ የተባሉ ታዋቂ የሃይማኖት መምህር እንደነበሩም ይነገራል። የመንደሩ ስያሜም ለእሳቸው በተሰጠው “ሾንኬይ” የሚለውን የክብር ስም ይዞ ቀጥሏል።

በመንደሩ የሚኖሩ አርጎባዎች በብዛት አርጎብኛ የሚናገሩ ሲኾን አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና አረብኛ ቋንቋዎችን በከፊል እንደሚናገሩ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያሳያል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here