መተማን በጥቂቱ፦

0
211

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መተማ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በምዕራብ ጎንደር ዞን ሥር ይገኛል። መተማ ዮሐንስ ከተማ አሥተዳደር፣ ገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳር እና የመተማ ወረዳን ያካትታል። የዞኑ ዋና ከተማ ገንዳ ውኃ ከባሕር ዳር 318 ኪሎ ሜትር፣ ከጎንደር ደግሞ በ162 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ሌላኛዋ የድንበር ከተማ መተማ ዮሐንስ ደግሞ ከገንዳውኃ 34 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝ የድንበር ከተማ ናት፡፡

የመተማ የአየር ንብረት ቆላማ፣ አማካይ የሙቀት መጠኑ ደግሞ እስከ 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል። የመሬት አቀማመጡ በአብዛኛው ሜዳማ ሲኾን አልፎ አልፎ ተራራማ እና ሸለቋማ ቦታዎች ይገኙበታል፡፡ ከአዲስ አበባ ካርቱም የሚያገናኘው ድንበር ተሻጋሪ ታላቅ የአስፋልት መንገድ የሚያልፍበት አካባቢ በመኾኑ ታላቅ የንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት ቀጣና ነው።

ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚኾን እና የውጭ ምንዛሬ ማምጣት የሚያስችሉ ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ አኩሪ አተረ፣ ማሾ፣ እጣን እና ሙጫ የሚመረትበት ቀጣናም ነው። በዞኑ ከሚገኙት ከተሞች ውስጥ የመተማ ዮሐንስ ከተማ ከሱዳኗ ጋላባት ከተማ ጋር የሚለያዩት በድልድይ ብቻ ነው።

ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን እንዲኹም ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በሚደረግ ጉዞ ዋና ማረፊያ በመኾን ያገለግላሉ። ሁለቱ ከተሞች የተያያዙ ከመኾናቸው የተነሳ የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሩ የጠነከረ ነው። አማርኛ እና አረበኛ ቋንቋዎች ደግሞ መግባቢያቸው ነው።

መተማ በርካታ የመስህብ ሀብቶች የሚገኙበት ቦታ ነው፡፡ አጼ ዮሐንስ ያረፉበት ቦታ፣ ወዲ አርባ፣ ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት እና የኢትዮ ሱዳን ድንበር የመሳሰሉ መስህቦች ይገኙበታል። እንዲኹም በዙሪያው የሚገኙ እንደ አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ የማኅበረ ስላሴ አንድነት ገዳም እና ጥብቅ ሥፍራ፣ የአጼ ቴዎድሮስ የትውልድ እና የትምህርት ቦታ የመሳሰሉ የመስህብ ሀብቶችን ለመጎብኘት የሚያመች ቦታ ነው።

በተጨማሪ አጼ ዮሐንስ ያረፉበትም በዚሁ ይገኛል። ከሱዳን የተነሱት ማህዲስቶች በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወረራ በማካሄድ የቀደምት ነገሥታት መናገሻ የነበረችውን ጎንደርን ማቃጠል መጀመራቸውን የሰሙት ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ጦራቸውን በማዝመት ወራሪውን መከላከል ችለዋል፡፡ በመጨረሻም አጼ ዮሐንስ ወራሪውን ጦር በመመከት ከዋና ምሽጉ መተማ አካባቢ ሲደርሱ ከማህዲስቶች በተተኮሰ ጥይት ተመትተው ሕይወታቸው ያለፈበት ቦታ ነው።

ይህ ንጉሠ ነገሥቱ ያረፉበት ቦታ ተከልሎ በቱሪስቶች እና ታሪክ አጥኝዎች እንደሚጎበኝ ከአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም የተገኘ መረጃ ያሳያል።

በዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here