“ልሂድ በወልድያ በአዋጅ መንገሪያው ሰው ጠራኝ መሰለኝ አቤት ልበለው ወንዙ ጥቁር ውኃ መቻሬ ሜዳው”

0
238

ባሕር ዳር: መጋቢት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወልድያ ከተማ የጁን እና ጎንደርን አጣምረው ያሥተዳድሩ በነበሩት በታላቁ ራስ ዐሊ ዘመን በ1777 ዓ.ም አካባቢ እንደተቆረቆረች የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ከየጁ ሥርዎ መንግሥት የራሶች ሀገር እምብርት የኾነችው ወልድያ፤ ገነቴ የሚባል ሥም እንደነበራት ይነገራል፡፡ በተራራዎች እና ኮረብታዎች የተከበበችው ወልድያ ከየተራራዎቹ የሚፈልቁት ወንዞች የሚፈጥሩት ሀሴት ገነቴ አሰኝቷት እንደነበር ነው በአፈታሪክ የሚነገረው።

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ የኾነችው ወልድያ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የሪጅኦፖሊታን ከተማነት ደረጃ አግኝታለች፡፡ ዕቴጌ ጣይቱ፣ የጁ እና ታላቁ ራስ ዓሊ በሚባሉ ክፍለ ከተሞችም ተዋቅራለች፡፡ ወልድያ ከተማ ሰዎች በፍቅር የሚኖሩባት ውብ ከተማ ናት። በደሴ – ደብረ ብርሃን እስከ አዲስ አበባ ድረስ፤ በደብረ ታቦር በኩል ከባሕር ዳር- ከላሊበላ፤ ከትግራይ፣ ከአፋር እና ከጅቡቲ የሚያገናኙ መስመሮች ስላሏትም ለንግድ እና ለኢንቨስትመንት የተመቸች ከተማ ናት፡፡

ለላሊበላ፣ ለአክሱም እና ለጎንደር ታሪካዊ ቦታዎች በቅርብ ርቀት የምትገኘው ወልድያ የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ በየብስ ብቻ ሳይኾን በአየር መጓዝ ለሚፈልጉም ምቹ አማራጯ ነው፡፡ በወይና ደጋ የዓየር ንብረቷ፣ በደግ እና እንግዳ አክባሪ ነዋሪዎቿ ምክንያት ወልድያ ለኑሮ እና ለጉብኝት ተወዳጅ ከተማ ናት፡፡

“ልሂድ በወልድያ በአዋጅ መንገሪያው
ሰው ጠራኝ መሰለኝ አቤት ልበለው

ወንዙ ጥቁር ውኃ መቻሬ ሜዳው” እንደተባለ መቻሬ ሜዳው፣ ወንዙ ጥቁር ውኃው፣ የቀደመ ታሪኳ፣ ዘመናትን የተሻገረ ድንቅ እሴቷ ያስናፍቃታል። ወልድያ ሆስፒታልን ጨምሮ የጤና ጣቢያዎች እና ክሊኒኮችም አሏት፡፡ ወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጆቿም የትምህርት ዕድል ብቻ ሳይኾን የሥራ ዕድልም ፈጣሪ ተቋማቶቿ ናቸው፡፡

የሼህ ሙሃመድ አል አሙዲን ስታዲዬም ለማኅበረሰቡ ስፖርትን በማነቃቃት እና የስፖርት ቱሪዝምን በማሳደግ በኩል እና የሥራ ዕድልን በመፍጠርም ትልቅ ሃብት ያላት ናት፡፡ በከተማዋ ውስጥ እና በዙሪያው የሚገኙ አብያተክርስቲያናት እና መስጊዶች የከተማዋ የሃይማኖት፣ የባሕል እና የታሪክ እሴት መለያዎቿ ናቸው።

ወልድያ ከተማ ሙስሊም ክርስቲያኑ ተዋድዶ እና ተከባብሮ የሚኖሩባት የፍቅር ከተማ ናት። በሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት አንዱ አንዱን አቅፎ እና አክብሮ የሚኖርባት የፍቅር ከተማም ናት፡፡ የረመዳን እና የጥር ሚካኤል በዓላት የመከባበር እና መተሳሰቡ ማሳያዎች ናቸው፡፡ የራስ ወሌ ብጡል፣ የጉግሳ ወሌ፣ የገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ፣ የአርቲስት አያሌው መስፍን፣ ሼህ ሙሐመድ አል አሙዲን እና የሌሎች ሥመ ጥር ሰዎች የትውልድ ከተማም ናት – ወልድያ፡፡

“እንጀራው ወልድያ እየተጋገረ ወጡ ጉባላፍቶ ሲሸተኝ አደረ” እየተባለ የሚገጠምላት፣ ባለቅኔዎች የሚወለዱባት፣ ደጎች እና አርቆ አሳቢዎች፣ ሀገር ወዳዶች፣ ፍቅርና ሰላም ጠባቂዎች የሚኖሩባት፣ የተራራ ግርጌ ውብ ሥፍራ ናት። ኢኒያ ተራራዎች ግርማን ይሰጧታል። በተጠንቀቅ ቆመው ንጉሥ እንደሚያጅቡ ጀግኖች ሁሉ በዙሪያዋ በጠንቀቅ ቆመው ወልድያን የሚያጅቧት ተራራዎች ውበቷን ያጎሉታል። ተናፋቂነቷን ከፍ ከፍ ያደርጉላታል።

“የማሽላው ሀገር አላ ገዶ ነው ጥንቅሹን ወልድያ ምን አበቀለው” እንዳሉ እነዚያ ጥበበኞች በዙሪያዋ እሸት እና ወተት የማይጠፋባት፣ የአላገዶ ማሽላ፣ የሳንቃ ሸንኮራ የበዛላት፣ የተራበ የሚጎርስባት፣ የተጠማ የሚጠጣባት፣ የታረዘ የሚለብስባት፣ እውነተኛ መውደድ የሚገኝባት የውቦች ከተማ ውብ ናት። ሂዱ ተመልከቷት። ደስታና ፍቅርን ታገኙባታልቸሁ። ደግነትን ታዩባታለችሁ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here