የቅርስ አምባዋ መቄት!

0
157

ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መቄት በኢትዮጵያ አስገራሚ እና ማራኪ የመሬት አቀማመጥ ከሚገኝባቸው ሥፍራዎች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ከቅርብም ኾነ ከሩቅ የሚታዩ ጫፋቸው እንደጦር ወደ ሰማይ የተቀሰሩ፣ በእጅ ተጠርቦ የተስተካከለ የሚመስል መውጫ እና መውረጃ ያላቸው ተራሮች እና አምባዎች፣ በአለቶች መካከል እንደ ስፌት እየተጥመዘመዙ ቁልቁል የሚንደረደሩት ወንዞች፣ አለፍ አለፍ ብለው የሚታዩ ረባዳ ቦታዎች ለጎብኝዎች ልዩ ውበትን ያላብሳሉ።

ከማራኪ አቀማመጡ እና ከገጠሩ ማኅበረሰብ ውብ አኗኗር በተጨማሪ መቄት በታሪካዊ ገዳማት መገኛነቱ ይታወቃል፡፡

የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው አካባቢው ከ18 በላይ ጥንታዊ ፍልፍል ገዳማትን በመያዙ “የታሪካዊ ገዳማት አምባ” በመባል ይጠራል፡፡ በመቄት እና አካባቢው የሚገኙ የተወሰኑ የመስህብ ሀብቶችን በማሳያነት እንካቹህ ብለናል።

➽. አቡነ አሮን ገዳም

የአቡነ አሮን ገዳም ከወልዲያ ከተማ 150 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ከምትገኘው የአግሪት መንደር በስተሰሜን ከሁለት ሰዓት የእግር መንገድ ጉዞ በኋላ የሚገኝ ገዳም ነው። ገዳሙ በ1330ዎቹ አቡነ አሮን በተባሉ የሃይማኖት አባት የተፈለፈለ ነው። የአቡነ አሮን ገዳም የዋሻ ውስጥ ፍልፍል ሲኾን የተለያዩ ክፍሎች፣ አምዶች፣ በሮች እና መስኮቶች አሉት፡፡

የመግቢያ በሩ ባለ ሁለት ተከፋች ሲኾን ከሰባቱ መስኮቶች አንደኛው በጣራው ላይ ይገኛል፡፡ የጣራው መስኮት መዝጊያ የሌለው በመኾኑ በፀሐይ ጊዜ በተወሰነ ሰዓት ብርሃን ያስገባል፡፡

አቡነ አሮን ዋሻውን ለመፈልፈል የተጠቀሙበት መጥረቢያ፣ የግብር ሙቀጫዎች፣ ጥንታዊ ስዕሎች፣ የብራና መጻሕፍት እና የአቡነ አሮን መቃብር በገዳሙ ይገኛል፡፡

➽. ቆላ ዋሻ ሚካኤል

ዋሻ ሚካኤል በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአቡነ ሙሴ እንደተሠራ ይነገራል። በውስጥ ግድግዳው ላይ የተቀረጹ የሰው፣ የበሬ፣ የፈረስ፣ የግመል፣ የውሻ፣ የድመት፣ የአንበሳ፣ የዝሆን፣ የቀጭኔ፣ የጉማሬ፣ የአጋዘን፣ የነብር፣ የቀበሮ እና ሌሎችም ስዕሎች የሚገኙበት ቤተ ክርስቲያን ነው።

ከ30 በላይ የባህታውያን መኖሪያ ዋሻዎች እና የአጼ ይኩኖአምላክ አያት መኖሪያ እንደኾነ የሚታመን ግቢ እና የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ይገኛሉ፡፡

➽. ናዙኝ ማርያም

ናዙኝ ማርያም በአቡነ ሙሴ በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት ከተፈለፈሉ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አንዷ ናት። በልዩ ጥበብ ከቀይ አለት የተቀረጸ ነው። ከመቄት ዋና ከተማ ፍላቂት 30 ኪሎ ሜትር ላይም ትገኛለች።

ናዙኝ ማርያም በአራት ማዕዘን ቅርጽ በልዩ የኪነ ህንጻ ጥበብ የተቀረጸች ሲኾን ይዘታቸው ተመሳሳይ የኾኑ ከ10 በላይ የማይከፈቱ መስኮቶች፣ በምሥራቅ አንድ የተከፈተ መስኮት፣ ሦሥት በሮች እንዲኹም አራት የተቀረጹ አምዶች በመያዝ እንደ ላሊበላዋ ቤተ ማርያም ከወጥ አለት የተፈለፈለች ናት፡፡

የመቄት ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ትግስት ወንዴ ወረዳው ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ ጀምሮ በርካታ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ቅርሶችን የያዘ አካባቢ መኾኑን ጠቅሰዋል።

መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ ቆላ፣ ወይና ደጋ እና ደጋማ የአየር ንብረት የያዘ ነው።

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እና ከዚያ በፊት እንደተገነቡ የሚነገርላቸው እንደ አቡነ አሮን፣ ደብረ ቀጢም፣ ፍቅርተ ክርስቶስ አንድነት ገዳም የመሳሰሉ ከ15 በላይ የሚኾኑ በአብዛኛው ከአንድ አለት ተፈልፍለው የተሠሩ የሃይማኖት ተቋማት እና ሰባት የቱሪስት መዳረሻዎች የያዘ ነው።

አካባቢው ለላሊበላ እና ለግሸን ማርያም አጎራባች እንደመኾኑ በሁለቱ ክብረ በዓላት ወቅት በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች ይጎበኙት እንደነበር ገልጸዋል።

በወረዳው፣ በማኅበረሰቡ እና በክልሉ መንግሥት አማካኝነት መዳረሻዎቹን የማልማት እና የቅርስ ጥገና ሥራ እየተሠራ ቢኾንም ከአካባቢው ካለው ሀብት አኳያ ሲታይ ግን ጅምር መኾኑን አንስተዋል።

ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ ለማግኘት አኹንም ግን የክልሉን መንግሥት እና የማኅበረሰቡን አቅም እንደሚጠይቅ አንስተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here