የኢንዱስትሪዋ ፈርጥ – ኮምቦልቻ!

0
189

ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምቾትን የሚሹ ሁሉ ይናፍቋታል። የከራማው ሀገረ ወሎ ሲነሳ ቀድማ ወደ አዕምሮ ትመጣለች። ሕዝቦቿ ፍቅር እና መዋደድ መለያቸው ነው። አብረን እንብላ እንጠጣ ደግሞ ባሕላቸው ነው።

“የቦርከና ውኃ ውስጡ ቦረቦር ጧት አይቼሽ ማታ ይመስለኛል ወር” እያሉ ተናፋቂነቷን በግጥም ያሞካሿታል።

ሰዎች ለሥራ ይተሙባታል። የጣሩም ይለወጡባታል። ከግለሰቦች አልፎ የልማት መነኻሪያ ናት። የኢንዱስትሪ ሰገነት ይሏታል። ብቻ ደግ ሕዝብ ከደግ ተፈጥሮ ጋር ተችሯታል። ለውጥን የፈለጉ ሁሉ መኖሪያቸው አድርገዋታል። ውቧ የኢንዱስትሪ መቀመጫ የኾነችውን ኮምቦልቻ። የኮምቦልቻ ከተማ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የምትገኝ በረከተ ብዙ ከተማ ናት። የጥንት ስሟም ቢራሮ እየተባለ ይጠራ እንደነበር አፈ ታሪኳ ይናገራል። ከተማዋ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት በ1928 ዓ.ም እንደተመሠረተችም ይነገርላታል።

በ1935 ዓ.ም ደግሞ የማስተር ፕላን ባለቤት ለመኾንም በቅታለች። የከተማዋን ስያሜ አስመልክቶ መላምቶች ያሉ ሲኾን “ካምፖሉቺያ” ከሚለው የጣሊያንኛ ቃል እንደመነጨ ሲነገር ትርጉሙም “መብራት ያለበት ሰፈር” ማለት ነው ይባላል። ይህ ስያሜ የከተማዋን መቆርቆር ከጣሊያን ወረራ ጋር የሚያገናኘው ሲኾን “ካምፖሉቺያ” በሂደት እየተቀየረ መጥቶ ከተማዋ አሁን የምትጠራበትን ኮምቦልቻ የተሰኘዉን ስያሜ ይዛ እንደቀጠለች ይነገራል።

የኢንዱስትሪዋ ፈርጥ የኮምቦልቻ ከተማ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የሪጆፖሊታን የከተማ ደረጃን አግኝታ በስድስት የገጠር እና በ14 የከተማ ቀበሌዎች እንዲሁም በአራት ክፍለ ከተሞች ተደራጅታለች፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ ተፈጥሯዊ አቀማመጧ በተራራማ ቦታዎች የተከበበች መኾኗ ልዩ ጌጥ የተሰጣት ከተማ ስትኾን ሜዳማ ቦታው ደግሞ በምቾት ያረፈችበት ነው። ከባሕር ጠለል በላይ በአማካይ 1 ሺህ 857 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ሁለ ነገሯ ምቹ የኾነች ከተማ ናት። በዙሪያዋ ከሚገኙት ተራራዎች መካከልም የየጎፍ ተራራ በከፍታው ትልቁ ነው።

የኢንዱስትሪ መዲናዋ ኮምቦልቻ ከአዲስ አበባ በ375 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣ የክልሉ ርእሰ መዲና ከኾነችው ባሕር ዳር ከተማ ደግሞ በ505 ኪሎ ሜትር፣ ከደቡብ ወሎ መሥተዳደር ዞን ዋና ከተማ ደሴ በ23 ኪሎ ሜትር ላይ እንዲሁም ከጅቡቲ ወደብ በ484 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

በከተማዋ ሥር የሚገኙ ሰዎች ሊመለከቷቸው፣ ሊጎበኟቸው እና ሊጠብቋቸው የሚገቡ የመስህብ ቦታዎች አሉ። በተለይም ቀልብን መያዝ የሚችሉ የእምነት ቦታዎች የሚገኙበት አካባቢ ነው። ትናንት የነበሩ ዛሬም ድረስ በእጅጉ የሚከበሩ እድሜ ጠገብ የእምነት ተቋማት ያሉባት ከተማ ናት ኮምቦልቻ።

“ሸርን እትፍ ብሎ መውደድ ከሚሞሽር
ሲያስቅህ አውሎ ሲያስቅህ ከሚያድር
ካቢሻገር አጭቶ ጠቢሳ እሚገድር
ዳሩን ከመሀሉ አንድ አርጎ ባንድ ክር
ህልቁ ሚኖርበት ከሰፊው መዲና ከደልዳላዉ ደብር” … ተብሎ የተዘፈነላት እና በርካታ የሕዝብ ሃብት የኾኑ ቅርሶች ያሉባትም ናት ኮምቦልቻ። ለአብነትም በ1872 ዓ.ም እንደተመሠረተ የሚነገርለት እና በኢትዮጵያ ብቸኛ ነው የሚባልለት የገደራ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ቤተ ክርስቲያን በዚሁ ከተማ ስር ይገኛል። በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ስም የተሠየመ መኾኑ ብቸኛ እንዲባል አስችሎታል። ይህ ዕድሜ ጠገብ ቤተ ክርስቲያን በውስጡ እጅግ ውድ የኾኑ ዘመናትን ያስቆጠሩ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እንዳሉትም ይነገራል።

ሌላው ምሥራቀ ምሥራቃት ልጎ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድነት ገዳምም የኮምቦልቻ ከተማ አንድ አካል ነው። ይህ ጥንታዊ ገዳም በአጼ ድልናኦድ ዘመነ መንግሥት እንደተመሠረተ ይነገርለታል። በ1879 ዓ.ም በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ደግሞ ዳሩ እሳት መሃሉ ገነት ተብሎ እንደተደበረም ይወራለታል። በ1939 ዓ.ም የእሳት አደጋ አጋጥሞት እንደነበርም መረጃዎች ያሳያሉ። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትዕዛዝ ታሪካዊ ይዘቱን ባለቀቀ መንገድም ጥገና ተደርጎለት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።

ኮምቦልቻ ስትነሳ አብሮ የሚነሳው ሌላው ጥንታዊው እና ታሪካዊው ቦታ መጅት መስጅድ ነው። ከከተማዋ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ልዩ ስሙ ሚጢ ቆሎ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የሚገኝ ነው። በዚህ መስጅድ የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል በድምቀት የሚከበርበት ቦታ ነው። የእምነቱ ተከታዮችም በረከትን ለማግኘት የሚተሙበት ታሪካዊ ሥፍራ ነው። በዚሁ ቦታ ላይ የአሹራ በዓልም በድምቀት ይከበራል።

ሌላው የዚህ አካባቢ ድንቅ ቦታ ዕድሜ ጠገቡ ዛውዮች የእስልምና ትምህርት ቤት እና መስጅድም አንዱ ነው። ከዛሬ 250 ዓመት በፊት እንደተመሰረተ ታሪኩ ያስረዳል። በቦታው የጥንት አባቶች መካነ መቃብር ይገኛል። መስጅዱ ሚጢግራር ከሚባለው ቦታ ላይ ይገኛል።

በኮምቦልቻ እና አካባቢው ከታሪካዊ እና ከእምነት ቦታዎች በተጨማሪ ሌሎች የመስህብ ቦታዎችም በርካታ ናቸው። የየጎፍ ተራራ ለኮምቦልቻ ልዩ ውበት ነው። ተራራው በለበሳቸው ጥብቅ የተፈጥሮ ዛፎች በሩቁ ሲመለከቱት ለኮምቦልቻ ከተማ እና አካባቢው ደጀን ነው። ከ28 በላይ አጥቢ የዱር እንስሳት በውስጡ እንደሚገኙ ይነገራል። ከ82 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎችንም በውስጡ አቅፎ ይዟል። የምኒልክ ድኩላ እና ጭላዳ ዝንጀሮ በጥብቅ ደኑ ውስጥ ደልቷቸው የሚኖሩበትም ነው።

ኮምቦልቻ የተቸረችው ብዙ ነው። ይህን ያዩ እና የተመለከቱ ኮምቦልቻን ይተሙባታል። በሰላምና በፍቅር ይኖሩባታል። ለለውጥ አመችነቷን የተረዱ ደግሞ ለሥራ ይሰለፍባታል። አምነው ወደሥራ የገቡባትም ለውጥን በተግባር ተርጉመውባታል። ለዚህ ደግሞ በከተማዋ የሚገኙ በርካታ ፍብሪካዎች ማሳያዎች ናቸው። ኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ መነኻሪያ የምትባለውም ለዚህ ነው። በኮምቦልቻ ሰው ፍቅር ነው። የተፈጥሮ ጸጋውም ልዩ ነው።

በአጠቃላይ ኮምቦልቻ ስትነሳ ፍቅር፣ መከባበር፣ አብሮነት፣ እና ኢንዱስትሪ ወደ አዕምሯችን ይመጣሉ። ለማንኛውም ኮምቦልቻን ከዚህ በላይ ማየት፣ መመልከት፣ ማልማት፣ ጸጋዎቿን መጠቀም ከሁሉም ይጠበቃል እላለሁ። በመረጃ ምንጭነት የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን እና የባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ላይ የተገኙ ሰነዶችን ተጠቅመናል።

ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here