ላሊበላ ለልደት በዓል የሚገቡ የውጭ እንግዶችን እየተቀበለች ነው፡፡

0
280

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መጭውን የልደት በዓል ለማክበር የላሊበላ ሆቴሎች ትኩረት ሰጥተው ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ በላሊበላ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ሆቴሎች በኮረና ቫይረስ፣ በሰሜኑ ጦርነት እና አሁን በአማራ ክልል ባለው ጸጥታ ችግር ምክንያት በችግር ውስጥ ቆይተዋል፡፡ ሆቴሎቹ አሁን ላይ ካሉበት መፋዘዝ ወጥተው ለልደት በዓል እንግዶችን ለመቀበል አንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡

የላሊበላ የሆቴሎች ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ ደምሳሽ ሆቴሎቹ የልደት በዓልን ምክንያት አድርገው የሚገቡ እንግዶችን ለመቀበል ሰፊ ዝግጅት እንዲያደርጉ መኾናቸውን ገልጸዋል። ማኅበሩ በዓሉን አስመልክተው ወደ ላሊበላ የሚገቡ በርካታ እንግዶች የሆቴል አገልግሎት ችግር እንዳያጋጥማቸው ከላሊበላ ከተማ አሥተዳደር የባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደኾነም ተናግረዋል።

አሁን ላይ ሆቴሎቹ አስፈላጊውን ግብዓት እንዲያሟሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊው በተለይ የውጭ ሀገር እንግዶች የኢንተርኔት አገልግሎት ችግር እንዳይገጥማቸው ሁሉም ሆቴሎች የዋይፋይ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ነው የገለጹት። ሌሎች ለእንግዶች የሚያስፈልጉ ነገሮች መሟላታቸውን የሚከታተል የተለያየ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።

እንግዶች ለልደት በዓል ወደ ላሊበላ እንዲመጡ ጥሪ እየደረገ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው የውጭ ሀገር እንግዶች ከወዲሁ ወደ ላሊበላ እየገቡ መኾናቸውን ገልጸዋል። በዓሉን የሚታደሙ የሀገር ውስጥ ፣ የውጭ ጎብኚዎችን እና ምዕምናን ለመቀበል ከከተማው ሆቴሎች በተጨማሪ የከተማዋ ነዋሪዎች የጽዳት እና ሌሎች ዝግጅቶችን እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በማኅበራቸው በኩልም 44 ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ዝግጁ እንዲኾኑ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። እንግዶች በዓሉን ለማክበር ወደ ላሊበላ እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here