አዊ እና መስህቦቿ!

0
219

ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢው ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ በርካታ ገዳማት፣ አድባራት እና አብያተ ክርስቲያናት፣ መካነ መቃብሮች እና ዋሻዎች፣ የብራና መጻሕፍት እንዲኹም ጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደኖች፣ የዱር እንስሳት እና የአዕዋፋት ዝርያዎች መገኛ እንደኾነ የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ከዚህም ባለፈም እንደ ዘንገና ሐይቅ፣

ጥርባ ሐይቅ፣ የትስኪ ፏፏቴ፣ የዶንዶር ፏፏቴ፣ የፋንግ ፏፏቴ መገኛም ነው።

ፋንግ ፏፏቴ ከቲሊሊ ከተማ በምዕራብ አቅጣጫ ሁለት ኪሎ ሜትር ገደማ የሚገኝ ማራኪ ቦታ ነው። ፋንግ የሚለው ስያሜ አፋፍ፣ ገደል፣ ጥልቅ ማለት እንደኾነም ይነገራል።

ሌላኛው የዶንዶር ፏፏቴ ሲኾን ከቻግኒ ከተማ በደቡብ አቅጣጫ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። በክረምት ወራት ከ35 ሜትር በላይ ከፍታ እየተምዘገዘገ የሚወርደው ፏፏቴ በተለዬ ኹኔታ ልዩ ስሜትን ይሰጣል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች ውስጥ ጥርባ ሐይቅም ይገኝበታል። ሐይቁ በአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ ከአገው ግምጃ ቤት ከተማ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋ ነው። አማካይ ጥልቀቱ 155 ሜትር እንደኾነ ይነገራል።

በልምላሜ በተከበበው ምድር አረንጓዴ መስሎ የሚታይ ማራኪ ሐይቅ ነው። ከአካባቢው ልምላሜ በተጨማሪ “ፊዳ” እና “ቻዙ” እየተባሉ የሚጠሩ የተራራ ሰንሰለቶች ለአካባቢው ተጨማሪ ልዩ ውበት አላብሰውታል። በፀደይ ወቅት ደግሞ ሐይቁን ለመጎብኘት ይበልጥ ተመራጭ ያደርገዋል።

ሌላኛው የተፈጥሮ ሀብት የኾነው መዳረሻ ደግሞ ዘንገና ሐይቅ ነው። ከእንጅባራ ከተማ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ማራኪ የመስህብ ቦታ ነው። አማካይ ጥልቀቱ 16ዐ ሜትር እንደኾነ ይነገራል፡፡

ሐይቁ በልምላሜ የታደለ መልክዓ ምድር፣ ዋሻዎች፣ ሃይማኖታዊ ቦታዎች፣ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው አዕዋፍት እና የዱር እንስሳት በሐይቁ ዙሪያ እና በቅርብ ርቀት መጎብኘት የምንችልበት ልዩ ቦታ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here