እምየ ወረኢሉ የዘውዲቱ ሀገር፣ የማህል እምብርቷ፣ የኢትዮጵያ ማህደር” የተባለላት ወረኢሉን በወፍ በረር!

0
316

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እየተባለች የምትወደሰው ወረኢሉ ወረዳ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ካሉት 24 ወረዳዎች መካከል አንዷ ናት። ከተማዋ በ20 የገጠር ቀበሌዎች እና በአራት የከተማ ቀበሌዎች ተዋቅራለች። በ1860 ዓ.ም በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት የተመሠረተችው ወረኢሉ ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ በሚወስደው መስመር 492 ኪሎ ሜትር፣ ከክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር 571 ኪሎ ሜትር እንዲኹም ከዞኑ ዋና ከተማ ደሴ በደቡብ 91 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

ወረኢሉ ቁጥር የሌላቸው የታሪክ ድንቅ አሻራዎች የተሸሸጉባት፣ የዓድዋ ታሪካዊ ድል መነሻ ምዕራፍ የኾነች እና የኢትዮጵያ እምብርት ናት። የዓድዋ መንፈስ አየሯን የሞላው፣ የአፍሪካ ኩራት የኾነው የጥቁር ሕዝቦች ድል ወርቃማ ታሪክ ትናንት የተፈጸመ እስኪመስል ድረስ ዛሬም በጉልህ የሚነገርባት የታሪካችን መዲና ናት።

ወረኢሉ እና ዓድዋ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ብቻ ሳይኾኑ የአንድ ታሪክ ተወራራሽ ባለቤቶችም ናቸው። ወረኢሉን ያለ አድዋ፣ አድዋን ያለ ወረኢሉ ማሰብ አይቻልም። የወረኢሉ ወረዳ በሰሜን በደሴ ዙሪያ፣ በደቡብ በጃማ፣ በምሥራቅ በሰሜን ሸዋ እና በአልብኮ፣ በምዕራብ በለጋንቦ እና ለገሂዳ ወረዳዎች ትዋሰናለች።

ከአጼ ናኦድ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የቤተ አማራ መናገሻ ዋና ከተማ ኾና ስታገለግል የቆየችው ወረኢሉ፣ መካነ ስላሴ የተወለዱበት፣ የልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን (የአጼ ኃይለ ሥላሴ) እናት ልዕልት የሽ እመቤት እና የልዑል ራስ መንገሻ ስዩም እናት የተወለዱበት እንዲኹም የአጼ ምኒሊክ ልጅ ንግሥት ዘውዲቱ ተወልደው የተዳሩበት ስፍራ ነው።

በአጠቃላይ፣ ለስመ ጥር እና ታላላቅ ነገሥታት መፍለቂያ የኾነች ምድር ናት። ወረኢሉ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያኖች የሚገኙባት ናት። ከእነዚህም መካከል በዓድዋ ጦርነት ወቅት ከአጼ ሚኒሊክ ጋር ዘምቶ በድል የተመለሰው ታቦተ ጽላት የሚገኝበት ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አጼ ልብነ ድንግል የተከሉት ንግሥተ ንግሥት ዘውዲቱ ለመታሰቢያቸው ያሰሩት ደብረንግሥት ማርያም፣ መካነ ስላሴ ብሎም ሌሎች ጥንታዊ ገዳማት ይገኙበታል።

ወረኢሉ፣ ቴክኖሎጂ ሳይስፋፋ በፊት ከበግ ፀጉር የሚሠራውን የስጋጃ ምንጣፍ ያስተዋወቀች ስትኾን በገጸ ምድር እና በከርሰ ምድር ሀብቷ የበለጸገች ናት። እንደ ነዳጅ ዘይት፣ ብረት፣ ታንታለም እና ሌሎች ማዕድናት መገኛም ናት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here