ባሕር ዳር: ሚያዝያ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተለያዩ ድምጻውያን ያዜሙላት፣ በኢትዮጵያን ሙዚቃ ኢንዱሥትሪ በደማቅ የሚጠቀሱ ድምጻውያን የፈሩባት፣ ‘አጥንት የሌላቸው’ የሚመስሉ ተወዛዋዦች የሚያረግዱባት ናት የዋግ ብሔረሰብ አሥተዳደር መዲናዋ -ሰቆጣ፡፡
“ካልተቀጠቀጠ አይበላም ቋንጣ የዋግ ሹሞች ሀገር እንዴት ነው ሰቆጣ” የተባለላት ሰቆጣ በኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥት የራሷ ቀለም ያላት ናት። የዋግ ሕምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብት፣ የታሪክ እና የባሕል ማዕከልም ናት፡፡ የአክሱም ሥርወ መንግሥት ማክተምን ተከትሎ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሥርወ መንግሥቱን በዛግዌ የመሠረተው መራ ተክለሃይማኖት መናገሻውን ላስታ ላሊበላ አደረገ፡፡
በኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንደጀመረም በታሪክ ተዘግቧል፡፡ እሱን ተከትሎም የዛግዌ ነገሥታት ከ300 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን እንደመሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሰቆጣ ከተማም የዚህ የታሪክ እና የጥበብ ማኅደር፣ የደግነት እንዲኹም የውበት ባሕር የኾነው የዋግ ሕዝብ መናገሻ ከተማ ናት፡፡
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት ባለሙያ አለፈ ዋኘው ስለ ሰቆጣ ከተማ ታሪክ፣ ባሕል፣ እሴቶች እና አኹናዊ ገጽታ አብራርተውልናል፡፡ ሰቆጣ ከተማ በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ነው የተቆረቆረችው፡፡ የመጀመሪያዋ ከተማ ከአኹኗ ሰቆጣ ሰሜናዊ አቅጣጫ ላይ በምትገኘው ፋጥዝጊ በምትባል ቦታ ላይ እንደነበርም ይነገራል፡፡
ከፋጥዝጊ የተሻለ ደልዳላ በመኾኗ ከተማዋ ወደ አኹኗ ሰቆጣ እንደተዛወረችም ነው የሚነገረው፡፡ በአገውኛ ሳቁጣ ማለት ስምንት ማለት ሲኾን ስምንት ጊዜ ችግሮች አልፋ እንደምትለማ እና እንደምትነሳ ከሚነገር ትንቢት የሚነሳ ስምም ነው፡፡ በሌላ በኩል ሳቁጡሩም ማለት እንዴት ሰነበትክ ማለት እንደኾነ እና አኹን ላይ ሰቆጣ የሚለውን ሥም እንደያዘች ይነገራል፡፡
ሰቆጣ ከተማ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በከተማ አሥተዳደር ትተዳደራለች፡፡ አራት ቀበሌዎች ያሏት ሲኾን ከ52 ሺህ በላይ ሕዝብም ይኖርባታል፡፡ የአገው፣ የአማራ እና የትግሬ ብሔረሰቦች ተሰባጥረው የሚኖሩባት ሰቆጣ ኽምጣና፣ አማርኛ እና ትግርኛ ቋንቋዎች በሰፊው ይነገሩባታል፡፡ ክችወይ፣ ወንድምወይ፣ እና መሰል በኾኑ የአጠራር እና የአቀራረብ ዘይቤያቸው የሚታወቁት ሰቆጣዎች የዋግን ሕዝብ ባሕል እና እሴት ዘካሪ እና አጠናካሪም ናቸው፡፡
ክችዎይ ማለት ሆዴዎይ፣ የኔው ማለት ሲኾን ማኅበረሰቡ ፍቅሩን፣ ውዴታውን እና አክብሮቱን ሲገልጽ ከልቡ መኾኑን እንደሚያመላክት አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ የሰው አክብሮቱ ልኬታ የሌለው የሰቆጣ ሕዝብ እንግዶቹ በልተው፣ ጠጥተው እንዲደሰቱለት በእጅጉ የሚጥር ሕዝብ ነው፡፡
“ሰቆጣ ጥሩ ነው ሥጋ በልቶ ጠጂ ትንሽ የሚያስፈራው በአትንኩኝ ነው እንጂ፡፡’ ሲባልም ሰቆጣዎች የሰው መውደድ የተሰጣቸው ልበ ገራገር እና ፍልቅልቅ ሕዝቦች የመኾናቸውን ያህል አትንኩኝ ባይነት እና ጀግንነትም አብሯቸው እንደኾነ ታሪክ እና ምግባራቸው ይመሰክራል፡፡ በዕድሜ እና በጋብቻ ኹኔታ እንዲኹም የክት እና የዘወትር የአለባበስ እና የአጊያጊያጥ ባሕላቸውን ጠብቀው የዘለቁት ዋጎች ይህ ባሕላቸው በመላ ኢትዮጵያ ተቀባይነት እና ተወዳጅነትን ያገኘ ነው።
አለባበስ፣ አጊያጊያጥ፣ አዘፋፈን እና እስክስታው በኢትዮጵያ የናኘው የዋግ ሕዝብ ባሕል በሰቆጣ እየረቀቀ፣ እየደመቀ፣ እያማረ እና እየተሞሸረ ለመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ ይደርሳል፡፡ ባሕሉን ለመጠበቅ እና ለማዳበርም ሰቆጣ የባሕል እና ኪነት ቡድኖችን እያፈራች ለመላ ኢትዮጵያ ታዳርሳለች፡፡ ሰቆጣ ከሌሎች አካባቢዎች የሚያገናኙ አማራጭ መንገዶችም አሏት፡፡ በዞኑ ማልማት ለሚፈልጉ ጥሬ እቃ ለማስገባትም ኾነ ምርትን ለማሰራጨት የሚያስችሉ አማራጭ መንገዶችም አሏት፡፡
ሰቆጣ ከተማ የ24 ሰዓት መብራት እና የስልክ ተጠቃሚ ናት፡፡ 10 የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የተጀመሩባት ስትኾን አንድ የትምህርት ኮሌጅም አላት፡፡ ማልማት ለሚፈልግ ባለሀብትም የኢንዱስትሪ መንደር ከልላ እየተጠባበቀች ነው፡፡ በዞኑ የማዕድን ሀብት፣ የፍየል ሥጋ እና ወተት፣ ከተከዜ ሐይቅ በሚመረተው ዓሣ እንዲኹም በማር ምርት አቅርቦቷ ሀብታሟ ሰቆጣ በዘርፉ ለሚሠማራ አልሚ ጥራት እና ብዛት ያለው ጥሬ እቃ አላት፡፡
የፍየል እና የዓሣ ቋንጣ በዘመናዊ መልኩ እየተዘጋጀ ለገበያ ይቀርብባታል፡፡ የፍየል ወተት በቆላማው አካባቢ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ሲኾን በሰቆጣም አልፎ አልፎ እየቀረበ እንደኾ ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡ ሰቆጣ ደርሶ ጠጅ ሳይቀምስ፤ እንዲኹም ነጭ እና ወለላ ማር ሳይይዝ የሚመለስ የለም፡፡ ጠጅ ቢሉ ብርዝ አምሮትን ነቅሎ እና የማርን ምንነት አውቆ የሚመለሱበት ሀገር ቢኖር ሰቆጣ እና አካባቢው ነው፡፡
ግድግዳው ከድንጋይ እና ከጭቃ እንዲኹም ጣሪያው ከእንጨት እና ከሣር የሚገነባው ባሕላዊ የ’ህድሞ’ ቤታቸው አኹንም ድረስ ተጠብቆ ያለና ሌላኛው የዋግ ሕዝብ መለያ እሴት ነው፡፡ በሰቆጣ ከተማም የሕዝቡን ባሕል እና ታሪክ እየዘከረ ይገኛል፡፡
ጀኔራል ኃይሉ ከበደን የመሳሰሉ በበረሀ፣ በጋራ እና ሸንተረር ወጥተው የሚወርዱ ጠላትን የሚያርበደብዱ፣ ለሀገራቸው እስከ መስዋዕትነትም የሚከፍሉ ጀግኖች የተወለዱባት፣ የመሯት እና የሞቱላትም ምድር ናት ሰቆጣ፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን