“ዋልያ ላይ እየተደረገ ያለው ነገር እንደ ትውልድ ያስወቅሳል”

0
91

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ኢትዮጵያ በዓለሙ ፊት ደምቃ ከምትታይባቸው ውብ የተፈጥሮ ጸጋዎች መካከል እንደኛው ነው። ሰማይን ተደግፈው የቆሙ የሚመስሉት ተራራዎች፣ ባዘቶ እየመሰሉ ከተራራው አናት ወደታች የሚወርዱ ፏፏቴዎች፣ ተፈጥሮ ያስዋባቸው ሸንተረሮች፣ በዚያ ሥፍራ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት የዓለምን ቀልብ ሲስቡ ኖረዋል። ዛሬም ይስባሉ።

ብዙዎች ባሕር እየሰነጠቁ፣ የብስ እያቋረጡ ወደ ዚያ ውብ ሥፍራ ተጉዘዋል። በደረሱም ጊዜ ባዩት ውበት ተደንቀዋል። ይህ ድንቅ ሥፍራ በድንቅነቱ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ ዓመታት አልፈዋል። ይህ ድንቅ ሥፍራ በዓመታት ሂደት ውስጥ ተደጋጋሚ የኾኑ ችግሮች ገጥመውታል። የገጠሙትን ችግሮችም እያለፈ መጥቷል። በተለይም ብርቅዬ እንስሳቱን ትኩረት ያደረገው ጥቃት የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ፈተና ነው።

ከሰሞኑ በተፈጸመ ጥቃት ዋልያዎች ተገድለዋል። ይህ ደግሞ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። የቱሪዝም ሚኒስትር ድኤታ ስለሺ ግርማ የስሜን ብሔራዊ ፓርክ ዩኔስኮ ድንቅ ብሎ ከመዘገባቸው ድንቅ ሥፍራዎች መካከል እንደኛው ነው ብለዋል። ዓለም ላይ ከሚኙ ድንቅ እና ማራኪ ሥፍራዎች መካከል መኾኑንም ተናግረዋል።

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ውብ የተፈጥሮ ገጽታን የተላበሰ፣ በውስጥ ብርቅዬ እንስሳትን የያዘ፣ ለኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ሰፊ ገቢ የሚያስገኝ ነው ብለዋል። በዓመት 30 ሺህ በላይ የሚኾኑ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ሲጎበኙት የቆዬ ድንቅ ሥፍራ መኾኑን ነው ያነሱት። ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያስገኝ፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መኾኑንም አንስተዋል።

በኢኮ ቱሪዝም ለተደራጁ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል። ለአካባቢው ነዋሪዎች ቱሪዝም እንደዋነኛ የገቢ ምንጭ ኾኖ ሲያገለግል መቆየቱንም አንስተዋል። የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ምንጭ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአካባቢው ወጣቶች በቱሪዝም ዘርፉ የራሳቸውን ሀብት እንዲያፈሩ እና በንግዱ ውስጥ ተሳታፊ እንዲኾኑ እንዳስቻለም ተናግረዋል።

የውጭ ባለሀብቶችንም የሳበ ድንቅ ሀብት መኾኑን ነው የገለጹት። ከቱሪዝም ውጭ በኾኑ ለማር ምርት እና ለሌሎች ሀብቶች ምንጭ መኾኑንም ተናግረዋል። ለኢትዮጵያ እና ለዓለም የሥነ መሕዳር መጠበቅ የራሱ የኾነ አስተዋጽኦ ያለው ሥፍራ መኾኑንም አንስተዋል።

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በቱሪዝም ብቻ ሳይኾን በሌሎች ዘርፎችም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም መሠረት ነው ያሉት ሚኒስትር ድኤታው የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ሳቢ ከኾኑት መካከል ቀዳሚው ነው ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ቱሪዝም መሠረት የኾነው ብሔራዊ ፓርኩ በተገቢው መንገድ መጠበቅ አለበት ነው ያሉት። ለቱሪዝም የሚሰጠው ጥቅም ቀጣይነት እንዲኖረው ፓርኩ በአግባቡ መጠበቅ አለበት ብለዋል። የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከዚህ በፊት በገጠሙት ችግሮች ምክንያት በዩኔስኮ በአደጋ ውስጥ ከሚገኙ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ ገብቶ እንደነበር አንስተዋል። በተሠራው ሥራ ግን ከአደጋ መዝገብ ውስጥ መውጣቱንም አስታውሰዋል።

በዋልያ ላይ እየደረሰ ያለው አደን እና ግድያ ከአደጋ መዝገብ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ነው የተናገሩት። በከፍተኛ ሥራ ከአደጋ መዝገብ ውስጥ የወጣው ብሔራዊ ፓርኩ ተመልሶ እንዳይገባ የአካባቢው ማኅበረሰብ በጥንቃቄ መጠበቅ አለበት ነው ያሉት።

የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያደርገው ጥበቃ ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል። ፓርኩ ከገጠመው ችግር እንዲወጣ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር ኾኖ እንደሚሠራም አስታውዋል። የዋልያ ጥበቃ ስትራቴጂ ተነድፎ መጽደቁንም ገልጸዋል። በዋልያ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ለማስወገድ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የሚኖሩ እንስሳት እንዲጨምሩ፣ ፓርኩ እንዲሰፋ እና የቱሪዝም እንቅስቃሴውም ከዚህ የበለጠ እንዲጨምር እንሻለን ነው ያሉት። ከዚህ በፊት ፓርኩ ላይ ገጥመው የነበሩ ችግሮች ታልፈዋል ያሉት ሚኒስትር ድኤታው አሁንም ችግሮችን መፍታት እንችላለን ነው ያሉት። ከአሁን ቀደም የነበሩ አስቸጋሪ ፈተናዎች እንደታለፉም አስታውሰዋል።

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ደኅንነት መጠበቅ ከቻልን የቱሪዝም እንቅስቃሴውን መጨመር እንችላለን ነው ያሉት። ዋልያ ቀላል ነገር አይደለም፣ ዋልያ የሀገር ምልክት ነው፣ ዋልያ የብሔራዊ ቡድናችን መጠሪያ ነው፣ የበርካታ ድርጅቶች ስያሜ ነው ብለዋል።

በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የነበረውን ስመ ጥር እንስሳ ማጣት የፓርኩን ገጽታ ያጠለሻል፣ የፓርኩን ብቻ ሳይኾን የሀገርን ገጽታ ያጠለሻል ነው ያሉት። እንደ ሀገር ተፈጥሮን ለመጠበቅ የተሰጠንን ክብር እና ዕምነትም ይሸረሽራል ነው ያሉት።

“ዋልያን መጉዳት የቱሪዝም እንቅስቃሴን ከመጉዳቱ ባለፈ እንደ ትውልድ እንወቀስበታለን” ብለዋል። ዋልያ በፓርኩ መካከል እና ገደላማ ሥፍራ ነው የሚኖር ያሉት ሚኒስትር ድኤታው እዛ ድረስ ተጉዘው ዋልያን ካጠቁ የፓርኩ ጥበቃ አስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ እንዳለ አመላካች መኾኑን ነው የተናገሩት።

ፓርኩ ተመልሶ ወደ በዩኔስኮ የስጋት መዝገብ ውስጥ እንዳይገባ ጥበቃ ያስፈልጋል ነው ያሉት። የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ለትውልድ የምናስተላልፈው ሀብት ነው ብለዋል። ስምምነቶችን ማክበር እና ፓርኩን መጠበቅ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

የሀብቱ ባለቤት የኾነው የአካባቢው ማኅበረሰብ በትኩረት መጠበቅ እንደሚገባውም ገልጸዋል። የዋልያ ጉዳይ ሁሉንም ሊያሳስብ የሚገባ ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here