ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14 /2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሐይቅ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ አንድነት ገዳም ከሐይቅ ከተማ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ በ2 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
በ862 ዓ.ም በአጼ ድልናኦድ ዘመነ መንግሥት በግብጻዊው ጳጳስ አቡነ ሰላማ ካልዕ እንደተመሠረተም ይነገራል፡፡
ገዳሙ በኢትዮጵያ ታሪክ ጥንታዊ ከሚባሉት ገዳማት የሚመደብ ሰው ሠራሽ የቱሪዝም ሀብት ነው፡፡ በርካታ የሀገረ መንግሥት ነገስታት እንደነ አጼ ይኩኖ አምላክ እና በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በኩልም ታላላቅ አባቶች የተማሩበት ገዳም እንደኾነም ይነገርለታል፡፡
ገዳሙ በቅዱሳት መጻሕፍት፣ የጽሕፈት ትምህርት እና በማኅበራዊ የምንኩስና ሕይዎት እና በተግባረ ዕድ የተደራጀ ስለመኾኑ ይነገራል።
ሐይቅ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ አንድነት ገዳም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ተማሪዎች፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው መነኮሳት በትምህርተ ሃይማኖት ሠልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ እንደተመረቁበትም ይነገርለታል፡፡
አባ ኢየሱስ ሞዓ በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ቆይታቸው መጽሐፍትን በማሰባሰብ፣ የትምህርት አደረጃጀቱን በማጠናከር እና የአሥተዳደር ማዕከል በማድረግ የተጫወቱት ሚና ታላቅ እንደነበርም ታሪክ ያስረዳል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በሐይቅ እስጢፋኖስ አንድ ታላቅ ቤተ-መጽሐፍት አቋቋመው ነበርም ይባላል፤ በርካታ መጽሐፍትንም ለገዳሙ እንዳበረከቱ ታሪክ ያስረዳል፡፡
የገዳሙ ተማሪዎች ለትምህርት እና ለጽሕፈት የተጉ እጅግ ጠቢባን እንደነበሩም ይነገርላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሐይቅ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ አንድነት ገዳም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሥነ መለኮት ወይም የመጀመሪያው ዩኒቨርሲት እየተባለ እንደሚጠራ የተናገሩት በደቡብ ወሎ ዞን የባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ ካሳ መሐመድ ናቸው፡፡
በኋለኛው ዘመን የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት መላሽ የተባሉት አጼ ይኩኖ አምላክም የሐይቅ እስጢፋኖስ ተማሪ ነበሩም ነው ያሉት፡፡
ይህ ገዳም በተፈጥሮው ጸጋን የተሞላ ቅዱስ ስፍራ በመኾኑ አይተው እና አድንቀው የማይጠግቡት፣ በውስጡ ያሉ በነፍስም በስጋም ታታሪ የኾኑ መነኮሳት የሚኖሩበት በመኾኑ ውበቱ እና ጸጋውን የከበረ አድርጎታል ይባልለታል፡፡
ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባለፈ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አልፎም እንደ ሀገር በርካታ በጎ ምግባሮችን በማድረግ በአካባቢው ካለው የሙስሊም ማኅበረሰብ ጋር በፍቅር እና በመተሳሰብ የሚኖር ለሐይቅ ከተማ የቱሪዝም እድገት ትልቅ ሚና ያለው ገዳም ነው፡፡
ሐይቅ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ አንድነት ገዳም በደቡብ ወሎ ዞን በደሴ ከተማ በቅርብ ርቀት በደሴ እና በወልድያ ከተማ መካከል ይገኛል፡፡ በመረጃ ምንጭነት የደቡብ ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ላይ የተገኙ ሰነዶችን ተጠቅመናል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን