የላሊበላ ቅርስ የእድሳት ፕሮጀክት ሂደት ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ።

0
139

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በቱሪዝም ሚንስትር ሰላማዊት ካሳ እና በፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ የተመራው የላሊበላ መካነ ቅርስ ጥገና ክትትል ኮሚቴ ምክክር አድርጓል።

በውይይቱ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የደብረ ሮሃ የቅዱስ ላሊበላ ገዳም የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ውይይቱ በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ በሚከናወነው የላሊበላ ቅርስ የእድሳት ፕሮጀክት ሂደት ላይ ያተኮረ ነው። የጥገና ሥራውን ለማከናወን የወጣው ዓለም አቀፍ የጨረታ ሂደት እና አጠቃላይ የጥገና ሥራው ላይ በሚደረገው ሳይንሳዊ ጥናት ዙሪያም ውይይት ተደርጓል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ የፈረንሳይ መንግሥት በቱሪዝም ዘርፍ እያደረገው ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የላሊበላ መካነ ቅርስ እንክብካቤ፣ የታላቁ ቤተመንግሥት እድሳት እና ብሔራዊ ሙዚየምን ለማዘመን የተጀመረውን ሥራ በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።

ለላሊበላ ቅርስ የእድሳት ፕሮጀክት ሂደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፣ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እና የላሊበላ ከተማ አሥተዳደርን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት አማካሪ ኮሚቴ መቋቋሙንም ገልጸዋል።

ከቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በውይይቱ የሥልጠና መድረክ እንዲመቻችም አቅጣጫ ተቀምጧል። የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ የላሊበላ ቅርስ እንክብካቤ የሚመለከቱ ሥራዎች እና የተጀመረው ጥናት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here