ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጅብ አስራ ማርያም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በወኮ ፍቅረ ሰላም ቀበሌ ልዩ ስሙ ጭቋላ በሚባል ቦታ ትገኛለች። ቤተክርስቲያኗን ለማግኘት ከለሚ ከተማ በምዕራብ አቅጣጫ 17 ኪሎ ሜትር በመኪና ተጉዘው ወኮ ፍቅረ ሰላም ቀበሌን ካገኙ በኋላ ደግሞ በእግር ከ2 እስከ 3 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠይቃል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ ከ15ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን በፊት በእሳቦ ውስጥ ሞረት በነበረው አቢሳ ጽዱ በሚባለዉ አቅኝ የተመሰረተች እንደኾነ መዛግብቶች ያስረዳሉ፡፡ የእንሳሮ ወረዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት በድረ ገጹ እንዳስነበበው ጅብ አስራ ማርያም የተባለችበት ምክንያት የደብሯ ካህናት ዳስ ሠርተው ለክብረ በዓሏ ቀን ወረብ ካቀረቡ በኋላ አገልግሎታቸውን ጨርሰው ከበሮዉን ከዳስ ውስጥ ረስተውት ሳያስገቡ ይሄዳሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ ያለችበት ቦታ ጫካ እና ጉራጉር የበዛበት ስለኾነ ጅብ በዚያ አካባቢ ሲንቀሳቀስ ከበሮውን ያገኝና ለመብላት ቆዳውን ሲግጥ ከበሮውን እንደነከሰ ይቀራል። ቄሶቹ ጠዋት ወደ ደብሯ ኪዳን ለማድረስ ሲሄዱም ጅቡን በዚህ ሁኔታ ያገኙታል፡፡
ከዚያም የአካባቢውን ነዋሪ ሕዝብ ጠርተው የታቦቷን ገድል እንዲመለከቱ ተደረጉ፡፡ ከዚያም ሕዝቡ እና ካህናት ከተወያዩ በኋላ “ይህች ታቦት ገድለኛ ናት፤ ከአሁን ቀደም ጠላት ሊያቃጥላት በመጣ ጊዜ ተሰውራ በማለፏ “ድንቡቅ ማርያም” የሚለው ስሟ ቀርቶ “ድብቅ ማርያም” ተብላ እንድትጠራ ተደርጓል።
አሁን ደግሞ ይህን ተአምር ከሠራች ተተኪው ትውልድ ተአምሯን እያስታወሰ እንዲኖር “ድብቅ” የሚባለው ስም ይቅርና “ጅብ አስራ ማርያም” ተብላ ትጠራ ብለው ወሰኑ። እነሆ እስከ ዛሬ ድረስም ጅብ አስራ ማርያም እየተባለች በመጠራት ላይ ትገኛለች፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን