ዞዝ አምባ

0
139

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዞዝ አምባ ለዓይን የሚማርኩ መልክዓ ምድራዊ ገጽታዎችን የያዘ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በለሳ አካባቢ የሚገኝ ቦታ ነው።

በዚህም በደን የተሸፈነ ማራኪ አምባ ላይ ከአንድ አለት የተፈለፈለ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፤ እሱም የዞዝ አምባ ጊዮርጊስ ነው። ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራው በቅዱስ ላሊበላ ሲኾን ገዳሙ የተመሠረተው ደግሞ በአጼ ይስሐቅ ዘመነ መንግሥት አባ አብሳሲ በተባሉ አባት እንደኾነ ይነገራል።

ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ቅኔ ማህሌት፣ ቅድስት እና መቅደስ እንዲሁም በግምት 40 ሜትር ጥልቀት ያለው የጸበል ቦታ “የሙሽራ ቤት” ተብሎ የሚጠራ የክርስትና ማንሻ ክፍል አለው፡፡

ከቤተ ክርስቲያኑ ጣሪያ ጋር የተያያዙ በደንብ የተዋቀሩ ስምንት ዓምዶች እና ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲናት ጋር የሚመሳሰሉ በር እና መስኮቶች አሉት፡፡ በዚህ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የብራና መጻሕፍት፣ ንዋየ ቅዱሳን፣ በራስ ወሌ የተበረከተ የብር መስቀል እና ሌሎች ቅርሶችም የሚገኙበት ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ በዞዝ አምባ ጊዮርጊስ ታኅሳስ 12 እና ሚያዝያ 23 ቀን ታላላቅ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ይከበራሉ።

ቤተ ክርስቲያኑ የሚገኝበት አምባ ላይ ሲኾን በሰሜን የስሜን ተራራዎችን፣ በምሥራቅ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደርን፣ በደቡብ እብናትን እና በምዕራብ ጎንደር ዙሪያን ከርቀት ለማየት የሚያስችል እና ልዩ ገጽታ ያለው ነው።

አካባቢውን መጎብኘት ለሚፈልግ ሁሉ ከጎንደር ከተማ በአርባያ በኩል 130 ኪሎ ሜትር፣ ከባሕር ዳር – አዲስ ዘመን – እብናት 200 ኪሎ ሜትር፣ ከምሥራቅ በለሳ ወረዳ ዋና ከተማ ጓሃላ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር መጓዝን ግድ ይላል።

በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ወደ ዞዝ አምባ በሚደረግ ጉዞ በየመንገዱ “ስውሩ ቤተ ሣሙኤል”በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ጅምር የዋሻ ውስጥ ቤተክርስቲያን፣ ደንቀዝ ልዩ ስሙ ጎመንጌ በተባለ ሥፍራ የሚገኘውን የአጼ ሱስንዮስ ቤተ መንግሥት ፍርሥራሽ እና ጎንድ ተክለሃይማኖትን መጎብኘት ይቻላል።

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና ኃይለማርያም ኤፍሬም በ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል እና የተፈጥሮ መስህብ በሚል ያሳተመውን መጽሐፍ በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here