ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስን ብሎም የጎጃምን ባሕል፣ ወግ፣ ትውፊት እና ታሪክ ለመዘከር ያለመ ሚያዝያን በደብረ ማርቆስ መርሐግብር በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
ሚያዝያን በደብረ ማርቆስ መርሐ ግብር በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን የቅርስ ጉብኝት በማድረግ የተጀመረ ሲኾን በዓደባባይ የባሕል ትዕይንቶች እና በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው።
ከሚያዚያ 27/2017 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም የሚቆየው ሚያዝያን በደብረ ማርቆስ ዓመታዊ በዓል የጎጃምን ባሕል፣ ወግ እና ታሪክ ሳይበረዝ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ታልሞ በከተማ አሥተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ አዘጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።
ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የቅዱስ ማርቆስ ዓመታዊ በዓል የዚሁ መርሐ ግብር አካል ሲኾን ኅብረተሰቡ በበዓሉ ዕለት በመገኘት ታሪካዊ በኾነው የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን እንዲታደም ጥሪ ተላልፏል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለን ጨምሮ የተለያዩ የክልል እና የከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን