ጥንታዊው የጎዜ መስጂድ

0
99

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፍራንሲስኮ ዛቪየር፣ ፋውቬሌ አይማየር እና በርትራንድ ሂርስች “የሙስሊም ታሪካዊ ስፍራ በአፍሪካ ቀንድ እና በኢትዮጲያ (2004-2010)” በሚለው የጥናት ጽሁፍ ላይ ጎዜ በወላስማ ሥርወ መንግሥት ከ13ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሊሠራ እንደሚችል ያመለክታሉ፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ በ1991 ባዘጋጀው መጽሄት ላይ ደግሞ መስጅዱን ያሠሩት የውጭ ዝርያ ያላቸው ሼህ እስማኤል ናስር በዚያን ጊዜ ካሠሯቸው አርባ ያህል መስጅዶች የመጨረሻው እንደኾነም ይነገራል፡፡

የስምንት መቶ ዓመት የዕድሜ ባለ ጸጋ የኾነው ይህ መስጂድ ከደብረ ብርሃን ከ90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሸዋ ሮቢት ከተማ ደግሞ በስተምዕራብ በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ መስጂዱ ከባሕር ወለል በላይ 1656 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኝ ተራራማ ጫፍ ላይ ነው ያለው፡፡

የመስጂዱ አሠራር እና ቅርጹ አራት ማዕዘን ሲኾን 7 ነጥብ 80 በ7 ነጥብ 80 ሜትር ስፋት አለው፡፡ ግድግዳው በደንብ በቦካ ጭቃ የተያያዘ የድንጋይ ግንብ ነው፡፡ የመስጂዱ ምሥራቅ አቅጣጫ ግድግዳ ላይ ወደ ውስጥ ገባ ያለ ሥፍራ ተሠርቶለታል። አገልግሎቱ ኢማሙ ሶላት የሚያደርጉበት ሲኾን ከፍታው 2 ነጥብ 10 ሜትር፣ ጥልቀቱ 1 ነጥብ 05 ሜትር እና 70 ሳንቲ ሜትር ስፋት አለው፡፡

የመስጂዱ ጣርያ አሠራር ሲፈተሸ ደግሞ በተለምዶ ህድሞ ተብሎ በሚታወቅ ሀገርኛ አሠራር ማለትም ጣርያውን በሚሸከሙ ክብ ምሰሶዎች ላይ በተጠረቡ እንጨት የጣውላ ወራጆች ተጠጋግተው ይደረደሩ እና በወራጆቹ ላይ መጀመርያ ኮረት ድንጋይ ተሞልተው በነዚህ ኮረት ድንጋይ በግርድፉ በተቦካ ጭቃ ተመርጎ ዙርያውን ትላልቅ ድንጋዮች ይደረደሩበታል፡፡

የግብረ ሕንጻው ግድግዳ እስከ 70 ሳንቲ ሜትር ድረስ ስለሚወፍር በአካባቢው ያለው ሞቃታማ የአየር ንብረት በአግባቡ በውስጡ የሚኖሩትን ምዕመናን እንዳያውክ ያደርጋል፡፡ ይህም ማለት በቀጥታ ከሚመጣው የፀሐይ ጨረር ውስጥ 30 በመቶው ብቻ ተሰብሮ ወደ ውስጥ እንዲገባ በማገዝ የውስጡን ቅዝቃዜ ማመጣጠን ማስቻሉ ነው፡፡

ምሰሶዎች በአንድ ረድፍ በሁለት ሜትር ልዩነት ተደርድረዋል። የተደረደረው ጣውላ በአካባቢው በተሠሩ ሚስማሮች ተያይዘዋል፡፡ እነዚህ ምሰሶዎች ወለሉ ተቆፍሮ የተተከሉ ሳይኾን ወለሉ ላይ በጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ እንዲቆሙ ተደርገው መሠራታቸው ከምስጥ እና ከአፈር ጋር በተያያዙ ተዛማች ችግሮች እንዳይበሉ ለመከላከል መኾኑን ልብ ይሏል፡፡

ሌላው ደግሞ አልፎ አልፎ የጨረቃን ብርሃን ተቀብለው በማንጸባረቅ እንደ መብራት የሚያገለግሉ ከአካባቢው ተመርጠው በውጨኛው ግድግዳ ላይ የተሰገሰጉ ነጫጭ ድንጋዮች ናቸው፡፡ ከመስጂዱ በስተ ደቡብ ከአጥሩ ጋር ተያይዞ የተሠራ ጣርያ የሌለው መለስተኛ አራት ማዕዘን ግንብ ይገኛል፡፡

አገልግሎቱም የመስጂዱ ተገልጋይ ሽማግሌዎች እና ደረሳዎች የግል መገልገያዎችን ለማስቀመጫነት እንደ ነበር የመስጂዱ ተገልጋይ ሽማግሌዎች ያስረዳሉ፡፡

ሕንጻው ዙሪያውን በድንጋይ በተሠራ አጥር የታጠረ ሲኾን አንድ የመግቢያ በር ብቻ አለው። እሱም በምስራቅ በኩል የተራራው መውጫ ላይ መደረጉ ሠሪዎቹ ለአገልግሎቱ ብቻ ሳይኾን ጥበቃ እና መከላከያን ከግምት ውስጥ በማስገባት ኾን ተብሎ ዲዛይን መደረጉን ያሳያል፡፡

መስጂዱ በኮረብታማ ተራራ ላይ እንደመገንባቱ በስተ ምሥራቅ ባለው ብቸኛ በር ለመዝለቅ አቀበቱን ለመውጣት እንዲያግዝ መወጣጫ ደረጃዎች የነበሩ መኾናቸው ዛሬም በዓመት አንድ ጊዜ ለሚከበሩት (ለአረፋ፣ ለኢድ እና ለመውሊድ) በዓላት መመልከት ይቻላል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here