ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴተ ጓንጉት ደብረ ምህረት ቅድሥት ክርስቶስ ሰምራ ገዳም በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን በፎገራ ወረዳ ጓንጉት በሚባል ቦታ ትገኛለች። ገዳሟ ከጣና ሐይቅ ምሥራቃዊ ዳርቻ እና ከወረታ ከተማ በምዕራባዊ አቅጣጫ 26 ኪሎ ሜትር የመኪና መንገድ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
ሸንበቆ በነፋስ የሚያደርገውን ረገዳ በማየት የተክሌ ዝማሜ የሚባለውን የወረብ ሥርዓት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያበረከቱት የአለቃ ተክሌም ሀገር ናት። (አለቃ ተክሌ የአለቃ ገብረ ሀና ልጅ ናቸው) የክርስቶስ ሰምራ ገዳም የፎገራ መስክ ላይ ተቀምጠው የጣናን ነፋሻ አየር እየማጉ መንፈሳዊ ሕይወትን እያጠኑ የሚኖሩባት ቅድሥት ሥፍራ ናት።
ጣናን ተንተርሶ በገጸ ምድር እና ከርሰ ምድር ሀብቱ የተንበሸበሸው፤ በቲማቲም፣ በሽንኩርት እና በበቆሎ እሸቱ የሚታወቀው ፎገራ፤ ሩዝን በሰፊው እያመረተ ለመላ ኢትዮጵያ ያከፋፍላል። የተንጣለለው ሜዳማው ሀገር ፎገራ መስኖውን ለሌሎች አካባቢዎች መላክ ባይችልም ምርት እና እሸቱን ለአዲስ አበቤዎች ሳይቀር ያደርሳል።
የፎገራ ምድር ከጣና ጋር እየተመጋገበ ቀደምት ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶችን አቅፎ እና ጠብቆ ያቆየም ምድር ነው።ከእነዚህ ውስጥም ክርስቶስ ሠምራ ገዳም ትጠቀሳለች። ቅድሥት ክርስቶስ ሠምራ በሸዋ ቡልጋ ቅዱስጊ በተባለ ቦታ በ848 ዓ.ም እንደተወለደች ይነገራል፡፡ ብሉይን እና ሐዲስን ተምራ ጨርሳለች። ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ለካህን ተድራ ልጆችንም አፍርታለች፡፡
ባለቤቷ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ቀሪ ምድራዊ ሕይወቷን በምናኔ አሳለፈች፡፡ በሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም እና በደብረ ሊባኖስ ገዳምም ኖራለች፡፡ ለዓመታት በባሕር ውስጥ ሥጋዋ አልቆ አጥንቷ እስኪታይና ዓሣ እስከሚመላለስባት ድረስ በድምሩ ለ39 ዓመታት መንፈሳዊ ተጋድሎ መፈጸሟን የሃይማኖቱ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ በምድር ላይ ረዘም ላሉ ዓመታት እንደኖረች የሚነገርላት ቅድሥት ክርስቶስ ሠምራ በክርስቶስ ሠምራ ገዳሟም ለ24 ዓመት መቆየቷ ተከትቧል፡፡
በስሟ የተሰየመችው ክርስቶስ ሠምራ ቤተ ክርስቲያን (ገዳም) የተመሠረተችው በ1223 ዓ.ም እንደኾነ ገድለ ክርስቶስ ሰምራ ያስረዳል፡፡ በዓሏም ግንቦት 12 እና ነሐሴ 24 ቀን በየዓመቱ ይከበራል፡፡ የግንቦቱ በዓል ከግንቦት 9 ቀን ጀምሮ የሚከበር ሲኾን በ11 ቅድስተ ሃና እና ቅዱስ ያሬድ ድጓ የጻፈበት ቦታ ላይ በዓሉ ይከበራል፡፡
እንደ ታሪኩ በገዳሙ አፅሟ ያረፈበት፣ ለክብሯ ከሰማይ የወረዱላት 7 አክሊሎች፣ ፅዋ እና ቁማ የፀለየችበት በትረ መስቀል ይገኛሉ፡፡ ክርስቶስ ሰምራን ለመጎብኘት በአካባቢው የተገኘ ሰው ቅድስተ ሃና፣ ጣና ቂርቆስ፣ ቅዱስ ያሬድ፣ ገዳመ ሥላሴ፣ ገዳመ ፅዮን፣ ገዳመ ቅድስት ቁስቋም፣ ቅዱስ ፋሲለደስ፣ ሪማ መድኃኒዓለም፣ ናርጋ ሥላሴ፣ ዳጋ እስጢፋኖስ እና ሌሎችም ገዳማትን እና ታሪካዊ ቅርሶችን መጎብኘት ይችላል፡፡
በውብ መልክዓ ምድራዊ የጣና ዳርቻ የአካባቢው አኗኗር ሥርዓት ተጨምሮበት ወደ ሥፍራው የሚጓዙ ሰዎች የሚመለከቷቸው ታሪካዊ ሥፍራዎች የክርስቶስ ሠምራ ገዳም ከመንፈሳዊ ሀብቱ ባሻገር የሀገር ውስጥ ቱሪዝም መገለጫ እንዲኾን አድርጓታል፡፡ የፎገራ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቻላቸው ካሴ እንዳሉት ገዳሟ ለባሕር ዳር እና ለጎንደር አየር ማረፊያዎች በቅርብ ርቀት ስለምትገኝ ከሩቅ ለሚመጡም ምቹ ናት፡፡ የየብስ እና የባሕር ትራንስፖርት በመጠቀምም መድረስ ይቻላል፡፡
👉 ከባሕር ዳር – በጣና ቂርቆስ – ክርስቶስ ሰምራ የጀልባ፣
👉 ከጎንደር – በጎርጎራ – ክርስቶስ ሰምራ የመኪና እና የጀልባ፣
👉ከደልጊ – ክርስቶስ ሰምራ የጀልባ፣
👉ከደብረታቦር – በወረታ – ክርስቶስ ሰምራ የመኪና ትራንስፖርት አማራጮች አሉ፡፡
በገዳሟ መብራት ለማስገባት የምሰሶ ተከላ እየተከናወነ መኾኑን እና ለውኃም የመስመር ዝርጋታ እንደሚቀረው ነው የገለጹት፡፡ ባለሀብቶች በቱሪዝም ዘርፍ እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል። የቅድሥት ክርስቶስ ሠምራ ዓመታዊ ክብረ በዓል እየተከበረ ነው። በርካታ ምዕምናንም በሥፍራው ተገኝተው እያከበሩ ነው። ይህችን ሥፍራ ሊያዩዋት እና ሊጎበኟት የተገባች ናት።
በዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን