የበርሃዋ ገነት!

0
74

ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የገንዳ ውኃ ከተማ ከአዲስ አበባ 889 ኪሎ ሜትር፣ ከባሕር ዳር 320 ኪሎ ሜትር፣ ከጎንደር ከተማ ደግሞ 158 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ የወደብ ከተማ ናት። ስያሜዋን ያገኘችው ደግሞ በከተማዋ አጠገብ በሚያልፈው የገንዳ ውኃ ወንዝ ስም እንደኾነ የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ወጣት እና ስፖርት ባሕል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረኪዳን መንጋው ነግረውናል።

በ1969 ዓ.ም በኢዲዩ እና በደርግ መንግሥት መካከል በመተማ ዮሐንስ ከተማ አካባቢ በተቀሰቀሰው ጦርነት ማኅብረሰቡ በመሸሽ ወደ አኹኗ ገንዳ ውኃ ከተማ በመስፈሩ በዚሁ ዓመት እንድትመሠረት ኾናል ነው ያሉት። ከ1969 እስከ 1996 ዓ.ም “ሸኽዲ” በሚል መጠሪያ ስትጠራ ቆይታለች ብለዋል። በ1996 ዓ.ም በክልሉ ዝክረ ሕግ ጋዜጣ ገንዳ ውኃ የሚለውን ስያሜ አግኝታለች። እስከ 2000 ዓ.ም ደግሞ የመተማ ወረዳ ዋና ከተማ ኾና አገልግላለች ነው ያሉት።

ግንቦት ወር 2000 ዓ.ም ላይ ወደ ከተማ አሥተዳደርነት ተሸጋገረች፤ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የዞን መቀመጫ እንድትኾን ተደርጓል ብለዋል። አኹን ላይ ከተማዋ በሦስት የከተማ ቀበሌዎች የተዋቀረች ሲኾን ከ80 ሺህ በላይ ሕዝብ ይኖርባታል ተብሎ ይታመናል። ገንዳ ውኃ በአብዛኛው ሜዳማ የመሬት አቀማመጥ አላት። ከባሕር ወለል በላይ ከ595 እስከ 1040 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች። ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያላት ሲኾን በተለይም ደግሞ በመጋቢት እና በሚያዚያ ወር የሙቀት መጠኑ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል።

በኢትዮ-ሱዳን መካከል በሚካሄደው የንግድ እንቅስቃሴ ደረቅ ወደብ ኾኗ ታገለግላለች ከተማዋ። አካባቢው እንደ ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ የመሳሰሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ እና የኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚያገለግሉ ምርቶች የሚመረቱበት እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእንስሳት ሃብት መገኛ የኾነው የምዕራብ ጎንደር ዞን ማዕከል በመኾኗ ከተማዋን ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለኢንዱስትሪ ተመራጭ እንድትኾን ያደርጋታል።

በዙሪያዋ እንደ አልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ፣ ጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ፣ በርሚል ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም እና ጥብቅ ደን፣ አንገረብ እና የመሳሰሉት ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቦታዎች መገኛ ናት ገንዳ ውኃ ከተማ።

ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here